ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት እና ለመተጋገዝ የምንጠቀምባቸው እንደ ደቦ፣ ዕድር እና ዕቁብ ያሉ ባህላዊ አደረጃጀቶች አሉ።
አደረጃጀቶቹ በደስታ እና በኀዘን ወቅት እርስ በርስ ለመደጋገፍ እና የፋይናንስ ቁጠባን ለማሳደግ ይረዳሉ። ከፍተኛ የሆነ የሥነ-ልቦና ድጋፍንም የሚቸሩ ጠንካራ ማኅበራዊ ዕሴቶቻችን ናቸው።
ደቦ፣ በተለይም በአርሶ አደሩ ዘንድ የእርሻ ሥራን እና የቤት ግንባታ ሥራዎችን በጋራ በመደጋገፍ ለመከወን ጥቅም ላይ ይውላል።
እነኝህ ቀደምት አደረጃጀቶች ለዘመናት ሲሠራባቸው የኖሩ፣ ከፍተኛ ጉልበት እና ጊዜ የሚጠይቁ ሥራዎችን በጋራ ለመወጣት የሚያስችሉ የኅብረት እና የበጎ ፈቃድ ሥራ ልማዶች ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተደራጀ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለሀገር ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል።
አገልግሎቶቹ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ከመቀነሳቸው ባለፈ፣ የማኅበረሰብ ውኅደትን እና ፍቅርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
በተጨማሪም ጊዜያዊ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የማኅበረሰብን ችግር በዘላቂነት በሚፈቱ መሠረታዊ ድጋፎች ላይ ያተኩራሉ።
ለአብነትም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የአረጋውያንን ቤት በማደስ፣ በደም ልገሳ እና የትራፊክ አገልግሎት ድጋፍ በመስጠት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የአረጋውያንን ቤት በማደስ ሒደት የተሻለ እና አስተማማኝ የመጠለያ ሁኔታ በመፈጠሩ የተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጤና፣ ደኅንነት እና ክብር ማስጠበቅ ተችሏል።
በደም ልገሳም በሕክምና ተቋማት የሚታየውን የደም እጥረት ለማቃለል ሰፊ ድጋፍ ተደርጓል።
በሌላ በኩል በዚሁ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሚሊዮኖች በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል የሚሳተፉበት ትልቅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ በስኬት እየተከናወነ ይገኛል።
በበጎ ፈቃደኞች የተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ፣ ለደን ሽፋን ማደግ እና ለግብርና ምርታማነት ከፍ ማለት አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።
ታዲያ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ለዛሬ ብቻ የሚውል ሳይሆን የሀገርን ነገ የሚያበራ የኅብረት ክንድ ውጤት ነው።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጡ የመሠረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች በመተግበሩ፣ የሀገርን የልማት ሸክም በመጋራት በኩል የራሱን ትልቅ ዐሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛል።
በተደራጀ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በዓይናም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: