የአንድ ወታደራዊ ተቋም እውነተኛ ውጊያ ዝግጁነትና ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚለካው በታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በተገነባበት የዶክትሪን መሠረት፣ ባለው የማይገሰስ ሕዝባዊ መሠረት እንዲሁም አባላቱ በሚላበሱት የሞራል ልዕልና ጭምር ነው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 87 መሠረት የሀገርን ሉዓላዊነት በጽናት የመጠበቅ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማረጋገጥ ህጋዊ እና ታሪካዊ አደራውን ለመወጣት የተቀረፁ 4 መሠረታዊ እሴቶችን አንግቦ ይንቀሳቀሳል።
እነዚህ የሠራዊቱን አስተሳሰብ፣ ወታደራዊ ሥነ-ምግባር እና ከሕዝብ ጋር ያለውን ጥልቅ ቁርኝት የሚወስኑ መመሪያዎች በዕለት ተዕለት ውሎው፣ በውጊያ ስምሪቱና በልማት ተሳትፎው ውስጥ በተግባር ደምቀው ይታያሉ።
የመጀመሪያው እሴት ከራስ በፊት ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት የሚለው መርሕ ሲሆን፣ ይህም ወታደራዊ አገልግሎትን የራስን ሕይወት መሥዋዕት በማድረግ የጋራ ደኅንነትን የማስጠበቅ የተቀደሰ ተግባር ያደርገዋል።
ሠራዊቱ አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ እና የከፋ የአየር ጠባይ ሳይበግረው ዳር ድንበርን በጀግንነት ሲያስከብር፣ በድንገተኛ የጎርፍ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ በመሆን የዜጎችን ሕይወት ሲታደግ፣ እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የልማት አጋርነቱን ሲያስመሰክር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለው ማኅበራዊ ቁርኝት ምን ያህል የጸና እንደሆነ ያሳያል።
ሁለተኛው እሴት የሆነው የተሟላ ስብዕናን ማረጋገጥ ደግሞ ከፍተኛ የሞራል ልዕልናን፣ ጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊንን፣ የሕግ የበላይነትን ማክበር እና ሰብአዊነትን የተላበሰ ሥነ-ልቦና መገንባትን ያካትታል።
በማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አባላቱ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የጦርነት ሕጎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የመንቀሳቀስ፣ ረዳት የሌላቸውን ወገኖች እና የሲቪል ተቋማትን ከጥቃት የመከላከል ግዴታቸውን በብቃት ይወጣሉ።
ይህንን የተሟላ ስብዕና ለማጎልበት እንደ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ እና የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ያሉ አንጋፋ ተቋማት ወታደራዊ ቴክኒክን ብቻ ሳይሆን ሥነ-ምግባርን እና አመራርነትን ያካተቱ ጥልቅ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ፤ የሕዝብ ንብረትን በቁጠባ መጠቀም እና ከሙስና የጸዳ አሠራርን መከተልም የዚሁ የዳበረ ስብዕና አካል ናቸው።
ሦስተኛው መሠረታዊ እሴት ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን መላበስ ሲሆን፣ ይህም የሠራዊቱን ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት እና ብሔራዊ ስብጥር በጉልህ የሚያሳይ መገለጫ ነው።
ተቋሙ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ተዋፅኦ በማንጸባረቅ ትንሿ ኢትዮጵያ ሆኖ የተዋቀረ በመሆኑ፣ ማንኛውም አባል በችሎታውና በሥራው ብቻ የሚመዘንበት፣ ብዝኃነት እንደ ውበት ተቆጥሮ የውስጥ አንድነት በጓዳዊነት ላይ የሚገነባበት የጸና ሥርዓት አለው።
ከዚህም ባሻገር ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በመሆን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች በሕግ በተሰጠው ሥልጣን በመቆጣጠር ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል።
አራተኛው እሴት በማንኛውም ግዳጅ የላቀ ውጤት ማምጣት ሲሆን፣ ሠራዊቱ የፀጥታ እና የሕግ ማስከበር ግዳጆቹን በብቃት ከመወጣቱ ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በሰፊው በመሰማራት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የሚያስጠራ የላቀ የሙያ ብቃት አስመዝግቧል።
ይህ የላቀ ውጤት በውጊያ መስመር ብቻ ሳይሆን በሎጂስቲክስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከጥቅም ውጭ የሆኑ ከባድ የሜካናይዝድ መሣሪያዎችን በራስ አቅም ሙሉ በሙሉ በማደስና የቴክኖሎጂ አቅምን በማሳደግም ይገለጻል።
እነዚህ እርስ በእርስ የተሳሰሩ አራት ቁልፍ እሴቶች የሠራዊቱን ሁለንተናዊ ማንነትና የሞራል ልዕልና ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
ማንኛውም የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና እና ሰላም ለማደፍረስ የሚነሳ ጠላት ወይም አፍራሽ ኃይል፣ ከሕዝብ ማህፀን በበቀለው፣ የሞራል ልዕልና በተላበሰው እና በራስ አቅም ቴክኖሎጂን ማደስ በሚችለው በዚህ የጸና አገራዊ ምሽግ ፊት ሲጋፈጥ አቅመ-ቢስነቱ እና ሽንፈቱ የተረጋገጠ ይሆናል።
የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ፣ የሕዝቦች ተዋፅኦ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና የቴክኖሎጂ በራስ የመቆም አቅም ተዋህደው መከላከያ ሠራዊታችንን የህልውና አስተማማኝ ምሽግ እና የብሔራዊ ክብር ምልክት አድርገውታል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: