Search

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን 591.6 በማምጣት በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነው ተማሪ ጃለል ግርማ

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 318

ካላቸው ላይ ቀንሰው እና አዋጥተው ያስተማሩት ወገኖቹን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ለዓመታት ቀና ደፋ ሲል ከርሟል።

የቤተሰቡን እና የሕዝቡን ያልተቋረጠ ደግነት ለመካስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ በጽናት እና በኃላፊነት ስሜት ሙሉ ጊዜውን በትምህርቱ ላይ በማተኮር እነሆ ዛሬ ለወርቃማው ውጤት በቅቷል - የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኙ ተማሪ ጃለል ግርማ።

ተማሪ ጃለል ይህንን ታሪካዊ ውጤት በማምጣቱ ከደገፉት ወላጆቹ እና ካስተማረው ሕዝብ አልፎ ኢትዮጵያን አኩርቷል።

ዜጎች ከመቀነታቸው ፈትተው በሚደግፏቸው የኦዳ ትምህርት ቤቶች በዕውቀት እየተኮተኮተ የመጣው ጃለል፣ ትውልዱ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ነው።

ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በቢሾፍቱ እና በአዳማ ኦዳ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በትጋት እና በብቃት ሲከታተል ቆይቷል።

ዘንድሮ በወሰደው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናም ከኢትዮጵያ ተፈታኝ ተማሪዎች ቀዳሚውን ውጤት (591.6) በማስመዝገብ ለተተኪዎች አርአያ፣ ለሀገራችንም ተስፋ መሆን ችሏል።

ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ብሩህ አዕምሮው እና አስደናቂ ውጤቶቹ መለያው የነበሩት ጃለል፤ ለዚህ ከፍተኛ ስኬት የበቃው ለዓመታት በዘለቀው ጠንካራ የትምህርት ትጋት፣ ባልተቋረጠ የቤተሰብ ክትትል እና በመምህራኑ የዕውቀት ድጋፍ መሆኑን ይመሰክራል።

ወደፊትም አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ባለው የ'ኤአይ' (AI) ዘርፍ ትምህርቱን በመከታተል ሀገራችንን እና ሕዝቧን በሙሉ አቅሙ ለማገልገል ቆርጦ ተነሥቷል።

በልጃቸው አስደናቂ ውጤት የተደሰቱት አባቱ አቶ ግርማ ኩሳ፤ ጃለል ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ትልቅ የማንበብ ፍቅር እንደነበረው እና የትምህርት አቀባበሉም ልዩ እንደነበር በኩራት ያስታውሳሉ።

የኦሮሚያ ልማት ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ በሀገር አቀፍ ፈተናው የተገኘው ይህ ውጤት ተማሪዎች በብቃት እና በሥነ ምግባር ታንጸው፣ የሀገር ፍቅር ኖሯቸው ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተሠሩት ሥራዎች ፍሬ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት፣ የልህቀት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መክፈቱ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ጥራት ያላቸውን ትምህርት ቤቶች በራስ አቅም መገንባት እና ማጠናከር ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የተስፋ በር እየከፈተ መሆኑንም የጃለል ውጤት ሕያው ምስክር ነው።

በሐምራዊት ብርሃኑ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: