Search

"ምንም የውኃ አበርክቶ የሌላት ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ፍጹም ተቀባይነት የለውም" - ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 227

ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የውኃ ምንጭ አበርክቶ ሳይኖራት ኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ታዋቂው የውኃ ሀብት ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።

ተመራማሪው እንዳብራሩት ግብፅ ወንዙን በብቸኝነት ለመጠቀም ያላት ስግብግብ ፍላጎት እና የምታራምደው ግትር አቋም ከራስ ወዳድነት የመነጨ የሺህ ዘመናት ስሁት ትርክት ነው።

ኢትዮጵያ የተቸራትን የተፈጥሮ ጸጋ እንዳትጠቀም ታሪካዊ ጠላቶች ከልማት ሊያስተጓጉሏት ቢሞክሩም፣ ኢትዮጵያውያን በቁጭትና በጀግንነት ወኔ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ማድረግ ችለዋል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ብርሃን ከማልበስ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን በኃይል በማስተሳሰር አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ትልምን እያሳካ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር ግድቡ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን ከደለል ክምችት፣ ከጎርፍ እና ከድርቅ አደጋ በመታደግ ዘርፈ ብዙ በረከት እያስገኘ መሆኑን ዶክተር ያዕቆብ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃን ጊዜው ባለፈበት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት በመቸንከር የጋራ ተጠቃሚነት ድርድሮችን እያስተጓጎሉ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿን በማስተባበር፣ በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ መሠረት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብት ተጠቃሚነትን በተግባር አስመስክራለች።

የሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የውኃ ልማት አቅም እና ዕውቀት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ መሆናቸውን ተመራማሪው ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ታችኞቹን ተፋሰሶች በማይጎዳ መልኩ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ብልፅግናን የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ዶክተር ያዕቆብ በአጽንኦት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: