የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡ፣ የዳያስፖራ አባላት እና ደንበኞች ፈቃድ የሌላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች እና ሕገ ወጥ የሐዋላ መረቦችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳሰበ።
ባንኩ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እነዚህ ሕገ ወጥ ተግባራት በኢትዮጵያ ሕግ በጥብቅ የተከለከሉ መሆናቸውን ገልጾ፣ በእነዚህ መንገዶች ገንዘብ መላክም ሆነ መቀበል ደንበኞችን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ፣ ለክፍያ መዘግየት፣ ለባንክ ሒሳብ ዕገዳ፣ እንዲሁም ለሕግ ተጠያቂነት እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የገንዘብ ዝውውር እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ ዜጎች ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶችን ብቻ እንዲጠቀሙም ባንኩ መክሯል።
ሕገ ወጥ መንገዶችን መጠቀም ላኪዎችንም ሆነ ተቀባይ ቤተሰቦችን አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለአስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል አስገንዝቧል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን 17 ሕገ ወጥ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት አዱሊስ መኒ ትራንስፈር፣ አማል ኤክስፕረስ፣ አማል ዩኤስኤ፣ አማና ኤክስፕረስ፣ አቫንቲ፣ አዋሽ ዳይሬክት፣ ባካል መኒ ትራንስፈር፣ ጁባ ኤክስፕረስ፣ ራስሚ ፔይ፣ ረማድ ፔይ (ወይም ረማዳ ፔይ ካህ)፣ ሽጌይ መኒ ትራንስፈር፣ ታጅ ፋይናንሻል ሰርቪስ፣ ታሳ ፔይ፣ ተወከል መኒ ሰርቪሰስ፣ ዩኤስዋየር፣ ወርልድ ዳይሬክት ሊንክ እና ዞላ የተሰኙ ድርጅቶች ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ደንበኞች የገንዘባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ገንዘባቸው አስተማማኝ በሆነ መንገድ መድረሱን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪሎች ብቻ እንዲጠቀሙ አጥብቆ አበረታቷል።
ማናቸውንም የገንዘብ ዝውውር ከማድረግ በፊት፣ የተመረጠው አስተላላፊ ድርጅት ሕጋዊ ስለመሆኑ በባንኩ ይፋዊ ድረ-ገጽ https://nbe.gov.et/mta/ በመግባት ማረጋገጥ እንደሚቻልም ብሔራዊ ባንኩ አስታውቋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: