ከብልሹ አሰራሮች ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ሥራ ላይ የዋለው "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት በመቅረፍና አሠራሮችን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።
በሀገራችን የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ እንደ ትልቅ እጥፋት የሚቆጠረውና የመደመር መንግሥት አገልግሎቶችን ሰው ተኮር ለማድረግ የሰጠውን ትኩረት የሚያረጋግጠው ይህ ሥርዓት፣ በኢትዮጵያ ባህል የተሟላ ማዕድን የሚወክለውን "መሶብ" የሚለውን ስም በመያዝ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቀናጅቶ በማቅረብ ስኬታማ እርምጃ እየተራመደ ይገኛል።
ይህ ዘመኑን የዋጀ አሠራር ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ድግግሞሾችን በማስቀረት የዜጎችን ጊዜና አላስፈላጊ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ መቆጠብ ችሏል።
ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ተጠያቂነትን የሚያስፍንና ተገልጋዮችን ፍፁም ባከበረ መንፈስ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በተቋማትና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከረና በተለይም ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ቅድሚያ በመስጠት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አሠራር መዘርጋቱን አስመስክሯል።
አሁን ላይ ይህን ዘመናዊ አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ አገልግሎቱን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሠራ ይገኛል።
ይህ ስትራቴጂክ እቅድ የሀገራችን የ10 ዓመት መሪ እቅድ፣ የመንግሥት የአስተዳደርና የአገልግሎት ፖሊሲን እንዲሁም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ የመሶብ አገልግሎት የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግሩ ዋና አካል እና ቀጣይነት ያለውን የመንግሥት ሥራዎች የማቀላጠፍ አቅም መሆኑን ያረጋግጣል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: