Search

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ የማኅበረሰባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መልሰናል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ቅዳሜ ነሐሴ 23, 2018 210

የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ መድረኩን በንግግር ባስጀመሩበት ወቅት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ያለውን እምቅ አቅም ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ የልማት ዕቅድ በማቀድ በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ ውጤታማ አፈፃፀም መመዝገቡን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፎች በተሠራው ዘርፈ ብዙ ሥራም የማኅበረሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ  ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ  የህግ የበላይነት ከማረጋገጥ ባሻገር የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለሳቸውንም አመላክተዋል።

በተያዘው 2019 በጀት ዓመትም በክልሉ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት በማፅናት የህግ የበላይነትን የበለጠ በማረጋገጥ እና ከውስጥና ከውጭ የሚታዩ የፅንፈኝነት ዝንባሌዎችንና አዝማሚያዎችን በማክሰም እንደ ሀገር የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አረጋ አረጋግጠዋል።

አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ ድክመቶቻችንን በማረምና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በመታገል የማኅበረሰባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሁንም መመለስ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ አሳስበዋል።

 

በተስፋሁን ደስታ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: