የጸጥታ ተቋሞቻችን የኢትዮጵያን አቅም በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባት መቻላቸውን ስናነሳ የመደመር መንግሥት የወሰደው የሪፎርም እንዲሁም የተቋማት ግንባታ አቅጣጫ በላቀ ደረጃ ፍሬ ማፍራቱን በተግባር የሚያሣይ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ ጥልቅ የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋሞቻችን በላቀ ሀገራዊ ዕይታ፣ በሕዝባዊ ወገንተኝነት እና በከፍተኛ መስዋዕትነት ታንጸው በማይናወጥ መሰረት ላይ ዳግም እንዲዋቀሩ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን የተበታተነ አሠራር በማስቀረት ተቋማቱን የሀገርን ዘላቂ ደኅንነት የሚያረጋግጡ የአንድ ትልቅ ማዕቀፍ አካላት አድርጎ በማቀናጀት ይህ የላቀ ስኬት ሊረጋገጥ ችሏል።
ይህ ስትራቴጂያዊ ማዕቀፍ የመከላከያ ሠራዊታችንን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን (NISS)፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርን (INSA) እንዲሁም የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በአንድ ላይ አጣምሮ ይዟል።
ውህደቱ ተቋማቱ በአስተሳሰብ፣ በአደረጃጀት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ የላቀ ልቀትን እንዲጎናጸፉ አስችሏቸዋል።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የሳይበር ደኅንነት ቴክኖሎጂዎችን ከወታደራዊ እና ከመረጃ ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር መቻሉ ተቋማቱ ከመከላከያነት ባለፈ መጪ ስጋቶችን አስቀድመው የመተንበይ እና በፍጥነት የማምከን አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል።
በዚህም በምድር፣ በአየር፣ በሳይበር እና በዲጂታሉ ዓለም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የሕዝቧን ሰላም የመጠበቅ አቅማቸው በአስደናቂ ሁኔታ ጎልብቷል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በየዓመቱ በቁልፍ ሀገራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት ሲያከሽፍ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ደግሞ ውስብስብ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በማክሸፍ የሀገርን ደኅንነት በንቃት አስጠብቋል።
በተመሳሳይ የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ አቅሙን በማዘመን ሳይንሳዊ የሕግ ማስከበር ሥራን ሲያሰፍን፣ የመከላከያ ሰራዊታችን ደግሞ ዘመናዊ የድሮን፣ የአየር እና የምድር ውጊያ ቴክኖሎጂዎችን በማስታጠቅ አቅሙን አዘምኗል።
ዛሬ ላይ እነዚህ የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋሞቻችን የዘመኑን የመረጃ፣ የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ልቀት በመታጠቅ የሀገራችን የጽናት መገለጫ እና የዕድገታችን ጠንካራ ከለላ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።
ቴክኖሎጂን ከተማረ የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ በመጠቀም ረገድ የተመዘገበው ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የጸጥታ ዋስትና ይበልጥ ያጠናከረ እና የዜጎችን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ትልቅ ሀገራዊ ድል ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: