Search

"በቀጣይ 5 ዓመታት የአዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እንተጋለን" - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

እሑድ ነሐሴ 24, 2018 292

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመታት እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት መላው የከተማዋ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል።

የከተማ አስተዳደሩ  ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አስተዳደሩ በስድስተኛው ዙር ምርጫ ሕዝቡ የሰጠውን ኃላፊነት መነሻ በማድረግ ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ወደ ተግባር በመግባቱ ቃሉን መፈጸም መቻሉን አስታውሰዋል።

በዚህም ነዋሪውን ተጠቃሚ ማድረግ እና ከተማዋን ተወዳዳሪ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የከተማዋ ነዋሪ እምነት አድሮበት ዳግም መርጦ ኃላፊነት እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

የዛሬው ውይይትም ነዋሪው የጣለባቸውን እምነት መነሻ ያደረገ እና በቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲሁም በ2019 በጀት ዓመት የእቅድ ዝርዝር ግቦች ላይ በማተኮር፣ የባለፉት አምስት ዓመታት አፈፃፀምን በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጁነት የሚረጋገጥበት መሆኑን አብራርተዋል።

አመራሩ በማንኛውም ሰዓት የመፈጸም ባህሉን ይበልጥ በማሳደግ ከፊት ሆኖ በመምራት እንዲሁም ሕዝቡን እና የልማት አጋሮችን በማስተባበር በሀገር አቀፍ የልማት ማንሰራራት ውስጥ የአዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም መድረኩ አስተዳደሩ በክረምት ከያዛቸው የ90 ቀን ሥራዎች ውስጥ የ60 ቀናቱን አፈፃፀም የሚገመግምበት መሆኑን ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል።

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: