ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጠናቀቀው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያ ሰላም ለጠቅላላው የአፍሪካ አህጉር የሚተርፍ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ ታላቅ ክስተት ነው።
ይህ ጉባኤ ዜጎችን ከመሠረቱ ያሳተፈ፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ የዳያስፖራ አባላትን ጨምሮ 4 ሺህ ተወካዮችን በማሰባሰብ የተከናወነ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ሂደት ነበር።
በዚህ ታሪካዊ ውይይት የውጭ ኃይሎች ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በራስ አቅም እና በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ የጸና የሰላም መሠረት መጣሉ፣ "የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ሰላም ነው" የሚለውን ጥልቅ ጂኦፖለቲካዊ እውነት በግልጽ አሳይቷል።
የምክክሩ ስኬት በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመላው አህጉር ላይ ቀጥተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ፣ ሂደቱ ለአፍሪካውያን አዲስ ተስፋን ፈንጥቋል።
ከዚህም ባለፈ ማኅበራዊ ትሥሥርን በማጠናከር የመጪውን ትውልድ ሥነ-ልቦና በጎ አቅጣጫ የሚያስይዝ ትልቅ ማዕቀፍ ፈጥሯል።
በምክክር ጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የታደሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እንዲሁም የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ፣ ይህ ሀገራዊ ስኬት ለአፍሪካ ያለውን ወሳኝ ድርሻ አስምረውበታል።
ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ሰላም የማይከፋፈል ባሕርይ እንዳለው ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ዝግጅት እና ጥልቀት ባለው ውይይት የፈጠረችው መረጋጋት ለአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የጋራ ብልጽግና ዋና ሞተር እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው የሺህዎችን ድምፅ በአንድ መድረክ ማሰባሰብን “ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ተግባር” ሲሉ ያወደሱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያውያን ሰላም ለቀጣናው ደኅንነት መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ አንጋፋ መሪዎች ለሐሳባቸው ማረጋገጫ አድርገው ያነሡት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ድሎችን ነው። የዓድዋ ድል አፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን በራሳቸው ጽናት በማሸነፍ ነጻነታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ያሳየበት ታሪካዊ ክስተት እንደነበር ሁሉ፣ ሀገራዊ ምክክሩም አፍሪካውያን የውስጥ ፖለቲካዊ ውዝግቦቻቸውን በራሳቸው ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ ማረጋገጫ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በዩኔስኮ የማይጨበጥ የዓለም ባህላዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የኦሮሞ ሕዝብ ሀገር በቀል የገዳ ሥርዓት በውይይት እና በጋራ መግባባት ውሳኔ የመስጠት ዕሴቱ ለዘመናዊ የዴሞክራሲ ሂደት እና ለሰላም ግንባታ ትልቅ አህጉራዊ አርዓያ መሆኑ በጉባኤው ተስተጋብቷል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እና የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መዲና መሆኗ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚገነባው ሰላም መላውን አህጉር የማነቃቃት አቅም እንዳለው ያረጋግጣል።
በምክክር የሚፈጠረው ሀገራዊ መግባባት መዋቅራዊ ጸጥታን ያጠናክራል። ይህ መረጋጋት በተራው በአፍሪካ ቀንድ የሚታየውን ሕገ-ወጥ ፍልሰት፣ የድንበር ተሸጋሪ ሽብርተኝነት እና የጦር መሣሪያ ዝውውር በመቀነስ የቀጣናውን የጸጥታ መዋቅር አስተማማኝ ያደርገዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ላይ ስትቆም፣ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶቿን በሙሉ አቅም በመጠቀም ለአፍሪካ ቀንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ትሥሥር፣ ለድንበር ተሸጋሪ ንግድ እና ለጋራ የኢኮኖሚ ውህደት መንገድ ትከፍታለች።
ሀገራዊ ምክክሩ በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የተደረጉ ሰፊ ውይይቶችን በማጠናቀቅ 400 መሠረታዊ የውሳኔ ሐሳቦችን ማቅረቡ ለወደፊት የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ግልጽ ካርታ አስቀምጧል።
ምክክሩ የጉዞው ማጠቃለያ ሳይሆን የረጅም ጊዜ የእርቅ እና የመደጋገፍ ሂደት መጀመሪያ ነው።
በመሆኑም በሂደቱ የሚገኘው ሀገራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት መሠረት ከመሆኑም በላይ፣ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ለአጠቃላይ አህጉሪቱ የጋራ ብልጽግና ታላቅ የማፋጠኛ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: