በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ውስጥ ደማቅ ዐሻራ ያሳረፈችው የመጀመሪያዋ በራስ አቅም የተሠራች አውሮፕላን “ፀሐይ” በ1928 ዓ.ም ወደ ሰማይ ስታንዣብብ የኢንዱስትሪ አብዮት ብርሃን በኢትዮጵያ ምድር ፈንጥቆ ነበር።
በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ልጅ በልዕልት ፀሐይ የተሰየመችው ይህች አውሮፕላን በጀርመናዊው መሐንዲስ ሉድቪግ ቬበር መሪነት ከኢትዮጵያውያን የካርፔንተሪ እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር በመሆን የተገነባች ድንቅ የጥበብ ውጤት ነበረች።
ታኅሣሥ 1928 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነሥታ 50 ኪሎ ሜትር ያህል በማብረር የመጀመሪያ የሙከራ በረራዋን በስኬት አከናውናለች።
ሆኖም ይህ አንጸባራቂ የቴክኖሎጂ እመርታ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት ተቀጨ። ግንቦት 1928 ዓ.ም ወራሪው ኃይል አዲስ አበባን ሲቆጣጠር አውሮፕላኗን እንደ ጦር ምርኮ ወደ ሮም ወሰዳት።
ያኔ የተጀመረው ያ የፈጠራ ጉዞ ባይቋረጥ ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ አፍሪካን አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ግዙፍ የአውሮፕላን ማምረቻ እና የከባድ ኢንዱስትሪ ማዕከል ባለቤት መሆን ትችል እንደነበር ማሰቡ በእያንዳንዳችን ውስጥ ጥልቅ ቁጭት ይፈጥራል።
ይሁንና ይህ ቁጭት በታሪክ ማኅደር ውስጥ ተዘግቶ አልቀረም። ከ88 ዓመታት የኢጣሊያ ቪኛ ዲ ቫሌ አቪዬሽን ሙዚየም ስደት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ መካከል በተደረገ ጠንካራ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ‘ፀሐይ’ ወደ እናት ምድሯ ተመልሳለች። ማረፊያዋንም ታሪኳን እና ክብሯን በሚመጥን መልኩ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አድርጋለች።
መመለሷ የታሪክ ፍትሕ መረጋገጡን ብቻ ሳይሆን የተነጠቅነውን የፈጠራ እና የታሪክ ኩራት ዳግም መቀዳጀታችንን ያበስራል።
ያለፈው ዘመን ቁጭት ዛሬ ላይ ትልቅ የይቻላል መንፈስን ወልዷል። የታሪካዊቷን ‘ፀሐይ’ መመለስ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በራሱ መሐንዲሶች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሠራት ‘ፀሐይ-2’ አውሮፕላን ይፋ መደረጓ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህች በዲጂታል አቪዮኒክስ የተገነባች ዘመናዊት ቀላል አውሮፕላን በሰው የምትመራ ከመሆኗም በተጨማሪ እንደ ድሮን ያለአብራሪ መብረር የምትችልበት ባለሁለት አገልግሎት አቅም አላት።
የ‘ፀሐይ-2’ መሠራት የመከላከያ ሠራዊታችንን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ቁመና እና ጠንካራ ተቋማዊ ዝግጁነት በግልጽ የሚያሳይ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው።
ይህ ስኬት ሠራዊቱ የውጭ የትጥቅ እና የመለዋወጫ ጥገኝነትን በመቀነስ የራሱን የበረራ ማሠልጠኛዎች እና የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች በሀገር ውስጥ ማዘጋጀት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን በተግባር አስመስክሯል።
ከዚህም ባሻገር የዚህች አውሮፕላን ግንባታ ለአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዕድገት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ መሠረት የሚጥል ነው።
አውሮፕላንን ከንድፍ እስከ ማምረት፣ መግጠም እና መፈተሽ ባለው ሙሉ የኢንጂነሪንግ ሒደት ማከናወን መቻሉ ለከባድ ኢንዱስትሪ ዕድገት አዲስ ምኅዳር ይፈጥራል።
ቴክኖሎጂን በ'ሪቨርስ ኢንጂነሪንግ' (Reverse Engineering) አሠራር በመበተን እና እንደገና በመንደፍ የውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን ለመቅረፍ የሚያስችል ሰፊ አቅም ተፈጥሯል።
የ‘ፀሐይ-2’ ማምረቻ ፋብሪካን ማደራጀት ከአቪዬሽን አልፎ ለሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የሚሆን የላቀ የብረታ ብረት፣ የኮምፖዚት ቁሳቁሶች እና የኤሌክትሮኒክስ መሠረተ ልማት እንድንገነባ ያስችለናል።
ይህም የዕውቀት ሽግግር ወደ ሲቪል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም በመፍሰስ በፈጠራ እና በኢኖቬሽን ምኅዳሩ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የፀሐይ ጉዞ ከትናንት መነጠቅ እና መገታት ተነሥቶ ዛሬ ላይ ወደ ላቀ ቴክኖሎጂያዊ ልዕልና የተሸጋገረበት መንገድ ለእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅ ትምህርት እና መነሳሻ ነው።
የጀመርነው መንገድ ባይቋረጥ ኖሮ የሚለው የትናንት ቁጭታችን ዛሬ ላይ በእኛው ልጆች ጥበብ እና ላብ ‘ፀሐይ-2’ ሆኖ አብርቷል።
ይህ ስኬት ጠንክረን ከቀጠልን ትልቅ የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ ማማ ላይ መድረስ እንደምንችል በተግባር ያረጋገጠ ደማቅ የይቻላል መንፈስ ማሳያችን ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: