Search

አንዲት እናት አራት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ በሰላም ተገላገለች

እሑድ ነሐሴ 24, 2018 279

በጎፋ ዞን ሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ሕፃናትን በሰላም ተገላግላለች።

በአሁኑ ወቅት እናቲቱ እና አራቱም ሕፃናት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሆስፒታሉ ገልጿል።

የማኅፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ግላንደ ጊሎ እንደገለጹት፣ በሆስፒታሉ ደረጃ ሁለት እና ሦስት ሕፃናትን በአንድ ጊዜ ማዋለድ የተለመደ ቢሆንም፣ በአንድ ወሊድ አራት ሕፃናትን በሰላም ማዋለድ መቻሉ በሆስፒታሉ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና እና የማኅፀን ሐኪም ደመቀ ይርጋው በበኩላቸው፣ እናቲቱ በነበረችበት አካባቢ መደበኛ የእርግዝና ክትትል ሳታደርግ ቆይታ፣ ያልተለመደ የጤና ሁኔታ ሲያጋጥማት ወደ ሆስፒታሉ መምጣቷን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ተገቢው ምርመራ ከተደረገላት በኋላም ለተከታታይ አምስት ቀናት በቅርብ የሕክምና ክትትል ሥር ቆይታ፣ አራቱንም ሕፃናት በሰላም መገላገሏን ከጎፋ ዞን ኮሙኑኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአራቱ ሕፃናት አባት አቶ ናፍቆት ቡሼ፣ ከዚህ ቀደም አምስት ሴት ልጆች እንዳሏቸው እና ባለቤታቸው በአሁኑ ወሊድ ደግሞ አራት ሴት ሕፃናትን መገላገሏን ተናግረዋል። በዚህም በድምሩ የዘጠኝ ሴት ልጆች አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች በመሆናቸው የተሰጣቸውን በደስታ እንደሚቀበሉ የገለጹት አቶ ናፍቆት፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ያላቸው አቅም ውስን በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

እናቲቱ ወ/ሮ አንድነት አማረ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም አምስት ልጆችን መውለዳቸውን ገልጸው፣ በአንድ ጊዜ አራት ሕፃናትን መገላገላቸው ለእርሳቸውም ያልተለመደና እንግዳ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ አንድነት፣ ለእርሳቸው እና ለሕፃናቱ ሕይወት የተረባረቡትን የሆስፒታሉ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች አመስግነዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: