የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከካናዳ እና ከሌሎች ሀገራት ለተውጣጡ የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ያዘጋጀው የስፖርት መርሐ ግብር የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት በአዲስ ስፖርት ፓርክ በድምቀት ተካሂዷል።
"የትውልድ ትስስር በእግር ኳስ" በሚል መርሕ በአሰልጣኝ አሸናፊ ግርማ አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ መርሐ ግብር ከ120 በላይ ከካናዳ የመጡ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና ወላጆች ተሳትፈዋል።
መርሐ ግብሩ ወጣቶቹ የሀገራቸውን ባህል፣ ታሪክ እና ተፈጥሮ በቅርበት እንዲያውቁ እንዲሁም በስፖርት አማካኝነት እርስ በርሳቸው እና ከሀገር ውስጥ እኩዮቻቸው ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲፈጥሩ ያለመ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ታዳጊዎቹ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መስህቦችን እና አዳዲስ የፓርክ ልማቶችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ጉብኝትም ስለ ሀገራቸው ባህል፣ እሴት እና ታሪክ የበለጠ እውቀት እንዲጨብጡ እንዲሁም ከትውልድ ሥረ መሰረታቸው ጋር በጽኑ እንዲገናኙ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ከካናዳ የመጡት የአሸናፊ ግርማ የስፖርት አካዳሚ እና የሰውነት ቢሻው የስፖርት አካዳሚ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ወዳጃዊ የእግር ኳስ ውድድር ያደረጉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደርን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በዚህ ሥነ ሥርዓት በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ እና በጉብኝቱ ለተሳተፉ ታዳጊዎች የዕውቅና ምሥክር ወረቀት፣ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ይህ ዓይነቱ ሀገራዊ መርሐ ግብር በውጭ ሀገር ያደጉ ህፃናት እና ወጣቶች ወደፊት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በልማት፣ በቱሪዝም እና በባህል ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑ ተመላክቷል።
በዋለልኝ ታምር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: