Search

ሀገራዊ ምክክሩ ለትውልድ ዘላቂ ትምህርት የሚያስጨብጥ ታሪካዊ ጉባኤ ነው፦ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት

እሑድ ነሐሴ 24, 2018 191

ሀገራዊ ምክክሩ የሕዝቡን የምክክር ባህል የሚያንጽ እና ለትውልድ ዘላቂ ትምህርት የሚያስጨብጥ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ሲሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን ገለጹ።

የሀገራዊ ምክክሩ ሒደቱ ከውጤቱም በላይ አስተማሪ የሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ በአመካካሪነት ያገለገሉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን እንደገለጹት፣ የምክክር ጉባኤው የተለያየ አቋም ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት እና ልዩ ልዩ ሐሳቦች የተንጸባረቁበት ነው።

ምክክሩ ለረጅም ዓመታት እየተንከባለሉ በመምጣት ወደ አለመግባባት እና ግጭት ሲመሩ የቆዩ አጀንዳዎች በጥልቀት የተመከረ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክሩ ሒደት ተመካካሪዎች አቋማቸውን፣ ፍላጎቶቻቸውን እና ስጋቶቻቸውን በነጻነት የገለጹበት ጉባኤ ነው ብለዋል።

ምክክሩ ከ400 በላይ ምክር ሐሳቦችን በማቅረብ መጠናቀቁን አንስተው፣ ተመካካሪዎች በአብዛኛው አጀንዳ ላይ ከስምምነት የደረሱበት፣ በጥቂት አጀንዳዎች ላይ የአማራጭ ሐሳቦች የቀረቡበት መሆኑን አስረድተዋል።

ተመካካሪዎች ለሀገር እና ትውልድ በማሰብ የቆዩ አቋሞቻቸውን ለውጠው ወደ መግባባት የመጡበት ውጤታማ ጉባኤ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘመናችን ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች ተለይተው መውጣታቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር ለመጪው ትውልድ ልዩነት ተፈጥሯዊ የሆነና መፍትሔውም ምክክር መሆኑን የሚያስገነዝብ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።

ከምክክሩ የተገኙ ሐሳቦች በፖሊሲ እና ሕግ ግብዓትነት የሚካተቱ መሆናቸውን አመልክተው፣ ለተግባራዊነታቸው በትኩረት መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም በምክክር ሒደቱ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በቀጣይም የበኩሉን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ከግጭት እና የኃይል አማራጭ ከመምረጥ ይልቅ ተቀራርቦ መምከር የበለጠ ጥረት፣ ትዕግሥት እና ብስለት የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ግጭት ከአስተሳሰብ ስለሚመነጭ ይህን አስተሳሰብ መቀየር የሚቻለው በምክክር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

ጫካ ገብተው የኃይል አማራጭ የተከተሉ አካላትም መፍትሔ የሚገኘው በምክክር እንደሆነ በመገንዘብ በውይይት ችግሮቻቸውን መፍታት እንዳለባቸው መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ማኅበረሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ፣ በሰላም ተንቀሳቅሶ መሥራት፣ መነገድና ምርቱን በገበያ መሸጥ እንዲችል ምክክርና ድርድርን እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: