በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አስተማማኝ እና ገለልተኛ የሆኑ የጸጥታ ተቋማት የማይተካ ሚና ያላቸው ሲሆን፣ የሪፎርም እርምጃዎችን በፅኑ መሠረት ላይ ለመትከልና የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተቋማት ግንባታ ቀዳሚውና ወሳኙ እርምጃ ነው።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶት ሲከናወን የቆየው የመደመር አስተሳሰብ የሪፎርም እና የተቋማት ግንባታ አቅጣጫ በተግባር ፍሬ ማፍራቱን በግልጽ የሚያሳየው ደግሞ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የደረሱበት ከፍተኛ የብቃት ደረጃ ነው።
ከመደመር አስተሳሰብ የሚመነጨው የጸጥታ ዘርፍ ሪፎርም ዋና ዓላማ ተቋማቱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ፣ ዘመናዊ፣ ሙያዊ እና የሕዝብንና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚችሉ ማድረግ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የነበሩ መዋቅራዊ ክፍተቶችን በመድፈን ተቋማቱ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ፍላጎት ሳይሆን በተገነቡበት ጠንካራ መዋቅር እና ህግ ብቻ እንዲመሩ ተደርጓል።
በዚህም የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማት አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ በሙያዊ ብቃት፣ በወታደራዊ ሳይንስ እና በሀገራዊ ፍቅር ላይ እንዲመሠረቱ በመደረጉ፣ የማንኛውም ወገን መጠቀሚያ ሳይሆኑ የሀገርና የሕዝብ የጋራ አለኝታ መሆን ችለዋል።
በዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ በሳይበር ደኅንነት እና በኢንቴሊጀንስ አቅም ላይ የተደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተቋማቱ በቀጣናው እና በአህጉራዊ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ያስቻለ ሲሆን፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ የሰው ኃይል ማፍራት መቻሉም የመደመር ሪፎርም ያፈራው ትልቁ ፍሬ ነው።
የጸጥታ ተቋማት ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዲስ መልክ በመቃኘት የሕዝብ አገልጋይነታቸውን እና ደኅንነት ጠባቂነታቸውን በተግባር በማስመስከራቸው የሕዝብ ደጋፊነት እና አመኔታ እንዲያድግ አድርጓል።
በተጨማሪም የጸጥታ ተቋማት መጠናከር የሰላም ዋስትና ብቻ ሳይሆን የሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ እድገት መሠረት በመሆኑ፣ የተገነባው የጸጥታ አቅም ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ማናቸውንም ስጋቶች በብቃት የመመከት አቅም በመፍጠር የሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የግብርና እንቅስቃሴዎች በሰላም እንዲከናወኑ አስተማማኝ ከለላ ሰጥቷል።
የመደመር መንግሥት የተከተለው የሪፎርም እና የተቋማት ግንባታ አቅጣጫ በወረቀት ላይ የቀረ መፈክር ሳይሆን በተግባር ትልቅ ፍሬ ያፈራ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን የጸጥታ ተቋማት የደረሱበት የአቅም ደረጃ ህያው ምስክር ነው።
ዘመናዊ፣ ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆኑ የጸጥታ ተቋማት መገንባታቸው የዛሬዋን ኢትዮጵያ ከስጋት የሚታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የሰላም እና የመረጋጋት መሠረት ሆና እንድትቀጥል በማድረግ ለነገዋ ሀገር ዘላቂ ኅልውና እና ብልጽግና አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: