የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ፣ የፖለቲካ ምህዳር እና የሕዝቦቿ እጣ ፈንታ ከዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባህር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሲሆን፣ የዓባይ እናት የሆነችው ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን ታሪክ ከህልውናዋ ነጥላ ማየት አትችልም።
ታሪካዊ አደናቃፊዎች እነዚህን የታሪኳ ማጠንጠኛ የሆኑ የውኃ ሀብቶች እንዳትጠቀም እጆቿንና አእምሮዋን በማሰር በርካታ ደባዎችን ሲፈጽሙ ቢቆዩም፣ ዛሬ ላይ ሀገራችን ታሪካዊ የቁጭት ማኅደሯን በመቀልበስ የልማትና የስኬት አዲስ ምዕራፍ ጀምራለች።
"ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል" የሚለውን የቆየ አባባል በመለወጥ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በራሷ አቅም በመገንባት የዘመናት የሕዝብ ሕልሟን እውን ያደረገችው ኢትዮጵያ፣ የውኃ ሀብቷን በቴክኖሎጂ በማበልፀግ ለራሷ አልፎ ለጅቡቲ፣ ለኬንያ እና ለሌሎች ጎረቤቶቿ የኃይል አቅርቦትን በመዘርጋት የአፍሪካ ቀንድ እውነተኛ የኃይል ቋትና የአህጉራዊ ብልፅግና መሪ መሆኗን በተግባር አስመስክራለች።
ይሁን እንጂ በሕዳሴው ግድብ የውኃ አጠቃቀም ሴራን ማፍረስ እና አህጉራዊ አጋርነትን ማጠናከር የተቻለ ቢሆንም፣ በታሪካዊ ስህተቶች የተወሰደው የቀይ ባህር በር ማጣት ጉዳይ አሁንም የሀገራችን ትልቁ ያልተመለሰ የህልውና ጥያቄ ነው።
ከአክሱም የስልጣኔ ዘመን አዱሊስ ወደብ ጀምሮ በምፅዋና በአሰብ ወደቦች በኩል ጠንካራ የባህር ኃይል በመገንባት የቀጣናው የንግድና የፖለቲካ መሪ የነበረችው ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ ለከፍተኛ የትራንዚት ወጪ፣ ለዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ዳርጓታል።
በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፍ ንግድ 80 በመቶው እንዲሁም ከኃይል ዝውውር 70 በመቶ በላይ በባህር የሚከናወን በመሆኑ፣ የቀይ ባህር ተጠቃሚነት የጂኦግራፊ ዕድል ብቻ ሳይሆን የሀገርን ዲፕሎማሲያዊ የመደራደር አቅምና የፖለቲካ ነፃነት የሚወስን ዋና ምሰሶ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በየዓመቱ ሚሊዮን ወጣቶችን ወደ ሥራ ዓለም የምታሰማራ እና የኢንዱስትሪና ኤክስፖርት ዕድገቷ በፍጥነት እየጨመረ የመጣ ሀገር የባህር በር ማጣቷ የንግድ መውጫ ፍለጋ ወይም የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን፣ የማደግ፣ የህልውና፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የቀጠናዊ ሎጂስቲክስን የማስፋፋት አጣዳፊ ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይና ለሎጂስቲክስ በየዓመቱ የምታወጣው ቢሊዮን ዶላር የሀገር ውስጥ ላኪዎችን ተወዳዳሪነት የሚያስቀር እና ለጤና፣ ለትምህርት እንዲሁም ለመሰረተ ልማት የሚሆንን ሀብት የሚበላ ከመሆኑም በላይ፣ የባህር በር አለመኖሩ ወታደራዊ ምስጢሮች በሌሎች ሀገራት እንዲያልፉ በማድረግ የሀገርን ደኅንነት ለአደጋ ያጋልጣል።
ስለሆነም ይህንን በታሪካዊ አጋጣሚዎች የተፈጠረ መዋቅራዊ አለመመጣጠን በዘመናዊ ዲፕሎማሲ፣ በሰላማዊ መንገድና በጋራ ኢኮኖሚያዊ ውህደት መርህ ማረም ለወደፊቱ ትውልድ የሚከፈል ግዴታ ነው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ የሌሎችን ግዛት የመንካት ወይም የግጭት ጥሪ ሳይሆን የባህር ዳርቻዎችን ወደ የጋራ ሀብትነት በመቀየር መላውን የአፍሪካ ቀንድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ መፍትሔ ነው።
መላው ሕዝባችን በሕዳሴ ግድብ ላይ ያሳየውን ጠንካራ አንድነት በማጠናከር የታሪክና የሕግ ማረጋገጫ ያለውን የባህር በር መብቱን በሰላማዊና ሕግን ባከበረ መንገድ ማረጋገጥ ይኖርበታል።
ደኅንነቷ የተጠበቀና በኢኮኖሚ የጠነከረች ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቀጣናው የመረጋጋትና የጋራ ብልፅግና ዋስትና በመሆኗ፣ ይህንን ጥሪ ተቀብሎ በጋራ ማደግ የአፍሪካ ቀንድ የወደፊት ስትራቴጂካዊ መስመር ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: