Search

የፅናትና የመስዋዕትነት ከፍታ በተዘረጋበት መረብ ያልተጠለፈው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና ለአፍሪካ ያበሰረው አዲስ ተስፋ

ሰኞ ነሐሴ 25, 2018 221

ዓባይ የሀገር ሲሳይ ተብሎ ሲዜምለት የኖረው የሕዝቦች የጋራ መስዋዕትነት እና የብሔራዊ ክብር ሕያው ተምሳሌት በመሆኑ ነው። በተራሮችና በሸለቆዎች መካከል ድንጋይ ፈንቅሎ የሚጓዘው ይህ ታላቅ ወንዝ፣ ይዞት የሚፈሰው ውኃን ብቻ ሳይሆን የትውልዶችን የማይበገር የፅናት ታሪክ ነው።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዞ በውጭ ሀገራት የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጫናዎች እንዲሁም የታሪካዊ አደናቃፊዎች የተወሳሰበ መረብ ተደቅኖበት የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም በማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ ሳይንበረከኩ የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው አቅም የመጠቀም ሉዓላዊ መብታቸውን በጥንካሬ አስከብረዋል።

ይህ ስኬት የኢትዮጵያውያንን እኛ እንችላለን ባይነት በተግባር ያስመሰከረ ብቻ ሳይሆን፣ መላው የአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በራሳቸው አቅም የራሳቸውን ዕድል መወሰን እንደሚችሉ ትልቅ የታሪክ ትምህርት ያበሰረና የተስፋ ብርሃን ያጫረ ታላቅ አህጉራዊ ኩራት ነው።

ኢትዮጵያውያን ባፈሰሱት ላብ፣ ጥረት እና ገንዘብ ከሰራተኛው እስከ አርሶ አደሩ፣ ከወጣቱ እስከ አረጋውያኑ የተቀናጀበት ይሄ የታሪክ ምዕራፍ የሕዝቦች አንድነትና ፅናት ምን ያህል ተአምር መስራት እንደሚችል ማረጋገጫ ነው።

ዓባይ ከተነሳበት ቦታ ጀምሮ በጉዞው ላይ ግዙፍ ተራሮችና ድንጋያማ ሸለቆዎች ሲያጋጥሙት ተራራውን ሰንጥቆ እንደሚያልፈው ሁሉ፣ ሕዝቡም የገጠሙትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎች በብቃት አልፎ ግቡን ማተቱን አሳይቷል።

ለዘመናት በቁጭት ሲነሳ የኖረው የዓባይ ታሪክ ዛሬ ላይ የፅናት ፍሬ አፍርቶ የጨለማችን ማብሪያና የብልጽግናችን መሠረት መሆን ችሏል። አባቶቻችን በዜማና በግጥም ያንጎራጎሩለትን ህልም በላቡና በአልሸነፍ ባይነቱ እውን ያደረገው የሕዝቦቻችን የማይበገር መንፈስ፣ ዛሬም በትውልዱ ደም ውስጥ እየፈሰሰ ይገኛል።

በጥቅሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቅ ዓላማና ፅናት ያለው ሕዝብ በምንም ዓይነት ማደናቀፊያ መረብ ውስጥ እንደማይወድቅ፣ መጨረሻውም ሁልጊዜም ብርሃንና ድል መሆኑን ያረጋገጠ ህያው ምስክር ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በራሷ ሙሉ አቅም ዳር በማድረሷ፣ አፍሪካውያን ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን አህጉራዊ ሀብት በራሳቸው ጥረት ማልማት እንደሚችሉ አዲስ የምስራችና የተግባር ትምህርት አስተምራለች።

 

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: