የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው እንደሚያነሱት፣ የመከላከያ ሠራዊት መለዮ ልዩ ክብር አለው።
መለዮው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ከሰንደቅ ዓላማው ጋር በማስተሳሰር ሁልጊዜ በመርህ ለሚሠራ የጸና ኃይል ትልቅ መታወቂያ ነው።
ይህ የክብር መጎናጸፊያ በውስጡ ታላቅ ሞገስን፣ ሥነ-ምግባርን እና ወደር የለሽ ጀግንነትን አቅፎ ይዟል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት መለዮውን ለብሶ እኛ ስናንቀላፋ የማይተኛ፣ ስንዝናና የማይዝናና፣ የበዓላት ጊዜውን ሳይቀር ሌት ተቀን ሕዝብን በመጠበቅ የሚያከብር ታላቅ የሕዝብ አለኝታ ነው።
የራሱን ሕይወት፣ ፍላጎት እና ጊዜ ሰውቶ ለኢትዮጵያ የቆመ መሆኑን መለዮው በየዕለቱ ይመሰክራል።
በመከላከያ ሠራዊታችን ልዩ ልዩ የሜዳ፣ የሰማይ፣ የባሕር እና የልዩ ኃይሎች መለዮዎች ቀለማት በስተጀርባ ጥልቅ የሆነ የሙያ እና የህልውና ምስጢር ይገኛል።
እነዚህ ቀለማት የየዕዙን ማንነት እና ተልዕኮ አጉልተው የሚያሳዩ ህያው ቋንቋዎች ናቸው። የምድር ኃይላችን የሚለብሰው አረንጓዴ እና የካኪ ቀለም መለዮ፣ ሠራዊቱ ከምድሪቱ ጋር ያለውን ጥልቅ ቁርኝት፣ አቧራ እና ጭቃ ሳይል ተራራ እና ሸለቆውን እያቆራረጠ እናት ሀገርን የመጠበቅ ጽናቱን ያሳያል።
የአየር ኃይላችን የሰማያዊ ቀለም መለዮ ደግሞ ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቆ የሚበርበትን ልዕልና፣ የኢትዮጵያን አየር ክልል ለማስከበር ያለውን የንስር ዓይን ንቃት እና ፍጥነት ይወክላል።
በአዲስ መልክ የተደራጀው የባሕር ኃይላችን ነጭ እና ጥቁር ሰማያዊ ቀለም መለዮ በበኩሉ፣ የሠራዊቱን የባሕር ላይ ሞገስ፣ ስልታዊ የውኃ ላይ ጥበቃ እና ጥልቅ ራዕይ የሚያንጸባርቅ ነው።
እነዚህን ዕዞች ይበልጥ ግርማ ሞገስ የሚያላብሷቸው የልዩ ኃይሎቻችን መለዮዎች ደግሞ የየራሳቸው ጥልቅ ትርጉም አላቸው።
የአየር ወለድ አባላት የሚለብሱት ማሩን ወይም ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ቆብ እና ልዩ የደንብ ልብስ የከፍተኛ ከፍታ ላይ ስምሪት ብቃትን፣ ፍጥነትን እና በማናቸውም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በጠላት ቀጣና ገብቶ ተልዕኮን የማጠናቀቅ ወኔን ያሳያል።
በሌላ በኩል የኮማንዶ ሠራዊታችን የሚታወቅበት ጥቁር መለዮ የማያወላውል ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጥንካሬን፣ ድንገተኛ እና ፈጣን እርምጃን፣ እንዲሁም በልዩ ስልታዊ ተልዕኮዎች ጠላትን የማንበርከክ ጽናትን አጉልቶ የሚያሳይ የጀግንነት ምልክት ነው።
ይህ የቀለማት እና የተልዕኮ ሁለገብነት በድንገት የተገነባ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ በደም፣ በዲሲፕሊን እና በጽናት ሲተላለፍ የመጣ የጀግንነት ቅብብሎሽ ነው።
መለዮው የሀገርን ደኅንነት ከማስጠበቅ አልፎ የጎረቤት ሀገራትን ሰላም እና መረጋጋት ለማስከበር የሚለበስ የዲፕሎማሲ እና የታማኝነት አህጉራዊ አምባሳደርነት ምልክት ሆኗል።
የሠራዊቱ ስም እና ዝና ከወሰን ተሻግሮ በምሥራቅ አፍሪካ እና በመላው አህጉር በክብር የሚጠራው በወታደራዊ ግርማ ሞገሱ ብቻ ሳይሆን፣ በአስቸጋሪ አህጉራዊ ተልዕኮዎች ውስጥ ገብቶ ሰላምን ማጽናት፣ የንጹሃንን ህይወት መታደግ እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የዚሁ ጀግና ሠራዊት መታወቂያ በመሆኑ ጭምር ነው።
ወታደራዊ አቅሙን ከሕዝባዊ ፍቅር እና ከከፍተኛ ሙያዊ ሥነ-ምግባር ጋር አዋህዶ መጓዙ፣ በሄደበት ሁሉ የማኅበረሰቦችን አመኔታ እንዲያተርፍ አስችሎታል።
የሠራዊቱ እውነተኛ ጥንካሬ በሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ከትላንት አባቶች ተረክቦ ለዛሬው እና ለነገው ትውልድ በሚያስተላልፈው ድል አድራጊነት እሴት ላይ የተመሰረተ ነው።
ታሪካዊ ፈተናዎችን በድል የመሻገር ጥበብ ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የጽናት ማኅተም ነው።
የትላንቱን ታሪካዊ ጽናት ከዛሬው የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ እና ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም ጋር በማዋሃድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የልማት እና የኢኮኖሚ ጉዞ አስተማማኝ ያደርጋል።
የሠራዊቱ ልዩ ልዩ መለዮዎች የቴክኖሎጂ፣ የውበት እና የሙያ መገለጫዎች ሲሆኑ፣ ቀጣናዊ የሰላም አስከባሪነቱ ደግሞ የአህጉራዊ ተፅዕኖው ማረጋገጫ ነው።
ከምንም በላይ ግን በእያንዳንዱ መለዮ በስተጀርባ ያለው የጀግንነት እሴት ከጥንት እስከ ዛሬ ሳይበጠስ የመጣ፣ ነገም የኢትዮጵያን ህልውና እና ብልጽግና ደግፎ የሚያቆም ጽኑ የትውልድ ቅብብሎሽ ነው።
ኢትዮጵያ ለማንም ጠላት ሸብረክ ሳትል የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ እንድትቀጥል፣ ለራሱ የኩራት ለአፍሪካ ደግሞ የብቃት ምንጭ የሆነውን ይህንን ዘመናዊ ሠራዊት የኢትዮጵያ መሆኑ የዜጎች ኩራት ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: