የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የበዓሉ አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አገኘሁ ተሻገር በ21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላቅ ያለ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጤት እንዲመዘገብ ከወዲሁ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገለጹ።
አፈ ጉባኤው እንዳመለከቱት በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህልና ልምዳቸውን በመለዋወጥ ኅብረ-ብሔራዊና ዲሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዘርፈ-ብዙ የኢኮኖሚ እድገት በጋራ እንዲቆሙ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በዓሉ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተጠናቅቆ አዲስ መንግሥት በተመሰረተበት፣ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት መሠረት በተጣለበት እንዲሁም የዲሞክራሲ ባህልን የሚያጎለብቱ በርካታ አገራዊ ሁነቶች በተከናወኑበት ማግሥት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ትርጉምና ገጽታ ይኖረዋል።
የገዳ ሥርዓትን ጨምሮ የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብቶች ባለቤት በሆነችው ታሪካዊቷ የጅማ ከተማ በሚካሄደው በዚህ በዓል፣ የሕዝቦች ወንድማማችነትና አብሮነት ከፍ ብሎ እንደሚንፀባረቅ ተጠቅሷል።
በዚሁ የምክክር መድረክ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወ/ሮ ባንቺይርጋ መለሰ የበዓሉን ረቂቅ መሪ ዕቅድ አቅርበው ጥልቅ ውይይት እንደተደረገበት ከምክር ቤቴ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: