Search

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሀገር ሰላም እና አብሮነት ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ነው፦ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ነሐሴ 26, 2018 241

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማትን በማስተባበር በሀራችን አብሮነትን ለመገንባት እና ሰላምን ለማፅናት እጅግ አበረታች ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የሕዝብን አንድነት፣ አጋርነት እና ወዳጅነት ለማጠናከር በተደረጉ ጥረቶች ውስጥ ጉባኤው የተጫወተው አዎንታዊ ሚና እጅግ የላቀ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እውቅና እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

ጉባኤው በሰላም እና በአብሮነት ችግሮችን በጋራ በማለፍ ታሪካዊ ድሎችን በአንድነት ማስመዝገቡን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በተለይም በቅርብ ጊዜ እየተከናወነ ያለውን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ጨምሮ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያበረከተው አስተዋጽኦ ለሀገር እና ለሕዝብ አለኝታነቱን የሚያሳይ እና ለብዙዎች ምሳሌ የሆነ መሆኑን አንሥተዋል።

በቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ያለፈውን ጉዞ በጋራ በመገምገም ጉድለቶችን መሙላት እና ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሰቡት።

በአሁኑ ወቅት ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቀው በትብብር እና በአንድነት በመቆም ሀገርን ማበልጸብ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ መሆኑን የመደመር መንግሥት ያምናል ብለዋል።

በመሆኑም ከልዩነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ በሰፊው በማተኮር፣ ከሁሉም በላይ ለሰላም፣ ለእውነት እና ለፍትሕ ምሳሌ የሆነ ማንነት በመገንባት ሕዝቡን ከቃል ባለፈ በተግባር መምራት እንደሚያስፈልግ ዶክተር መሐመድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: