ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ምህዳር በከፍተኛ ፍጥነት እየተሸጋገረች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ከጥቃት የሚከላከል አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ጸድቋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ለኢበቢሲ እንዳረጋገጡት፤ ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ የወጣው "የቁልፍ መሠረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት አዋጅ" ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ የሚገባው ከአንድ ዓመት የዝግጅት ጊዜ በኋላ ይሆናል።
ይህ የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ የተሰጠው በዋናነት በተቋሙ በኩል ዝርዝር የሕግ ማዕቀፎችን፣ የሀብት መለያ ስታንዳርዶችን እና የፈንድ አስተዳደር መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ነው።
በተጨማሪም በ12ቱ የቁልፍ መሠረተ ልማት ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ተቋማት የውስጥ የሳይበር ደኅንነት ማዕቀፍ እንዲያዘጋጁ፣ የስጋት ዳሰሳ እንዲያካሂዱ እና የሰው ኃይላቸውን እንዲያደራጁ ዕድል ለመስጠት መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አዲሱ አዋጅ የግሉ ዘርፍ በሳይበር ደኅንነት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፍ ትልቅ በር መክፈቱን እና ተሳትፎው በጠበቀ ቁጥጥርና ደንብ የሚመራ መሆኑን አንስተዋል።
የግል አገልግሎት አቅራቢዎች ከመደበኛ ንግድ ፈቃድ በተጨማሪ በተቋሙ የሚሰጥ ልዩ የሙያ ፈቃድ ሊኖራቸው ይገባል።
ይህ ፈቃድ የሚሰጠውም ለተቋማቱ እና ለባለሙያዎቻቸው ጥብቅ የማንነት እና የደኅንነት ማጣራት ከተደረገ በኋላ ነው።
ከዚህም ባሻገር፣ ለሀገር ብሔራዊ ደኅንነት ሲባል እጅግ ስስ በሆኑ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የግሉ ዘርፍ እንዳይሳተፍ ገደብ የሚጣል ሲሆን፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችም የተረጋገጠ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ያስገድዳል።
የልዩ ሙያ ፈቃድ የደኅንነት ማጣራት በማድረግ የግል ተቋማቱ እና ባለሙያዎቻቸው ጥብቅ የሆነ የማንነት አእና የደኅንነት ማጣራት በማድግ ፍቃድ የሚሰጣቸው ይሆናል።
ለሀገር ብሔራዊ ደኅንነት ሲባል እጅግ ቁልፍ በሆኑ መሠረተ ልማቶች ላይ የግሉ ዘርፍ እንዳይሳተፍ ገደብ እንደሚጣልም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በአዋጁ መሠረት፣ በቁልፍ መሠረተ ልማት ጥበቃ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎች "የተረጋገጠ ሙያ" ያላቸው መሆን አለባቸው።
ይህም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ወይም እውቅና በተሰጣቸው ተቋማት የሚሰጥ የምስክር ወረቀት መኖር እንዳለበት ያስገድዳል።
የሕግ ማዕቀፉን በውጤታማነት ለማስፈጸም "የሳይበር ደኅንነት ፈንድ" የተሰኘ አዲስ የፋይናንስ ምንጭ ይቋቋማል።
ፈንዱ ከተቋማት መዋጮ፣ ከአገልግሎት ክፍያዎች እና ከአስተዳደራዊ ቅጣቶች የሚሰበሰብ ሲሆን፤ ለአቅም ግንባታ፣ ለምርምር፣ ለሀገራዊ የሳይበር ልምምዶች እና ተቋማት በጋራ የተደራጀ የመከላከል አቅም እንዲገነቡ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ይውላል።
ሌላው ዋና የሕጉ ክፍል ደግሞ የሪፖርት ግዴታ ሲሆን፣ ማንኛውም የቁልፍ መሠረተ ልማት ተቋም የሳይበር ጥቃት ሲያጋጥመው በ48 ሰዓታት ውስጥ ለተቋሙ ማሳወቅ ይኖርበታል።
ይህንን ግዴታ ባልተወጡ ተቋማት ላይም አስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶች እንደሚጣሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የቁልፍ መሠረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት አዋጅ ዓላማው ተቋማትን ለመቅጣት ሳይሆን፣ ሀገራዊ የመከላከል አቅምን ማጠናከር ነው።
የግሉን ዘርፍ ዕውቀትና የፈጠራ አቅም ከመንግሥት ቁጥጥር ጋር በማጣመር፣ አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ኢኮ-ሲስተም ለመፍጠር የተነደፈ የሕግ ማዕቀፍ ነው።
ተቋማትም የተሰጣቸውን የ1 ዓመት የዝግጅት ጊዜ በመጠቀም ራሳቸውን ለአዲሱ አሠራር ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ ለኢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: