"እምነትን በተግባር፣ ሰላም እና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተካሄደ ነው።
በጌባኤው ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ፣ የእምነት ተቋማት እና የሃይማኖት መሪዎች የሀገራችን የሞራል እና የሥነ-ምግባር ዋና ጠባቂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው የእምነት ተቋማት ለዘመናት የሕዝብን ስብዕና ሲገነቡ የኖሩ መሠረቶች በመሆናቸው በጨለማ ውስጥ ብርሃን በመሆን የማስተማር፣ የማረም እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ የሕሊና
መዛሎችን እና የጥፋት መንገዶችን በሐሳብ ልዕልና የማቅናት ተቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አክለውም ከውጭ በሚመጡ አጉል ልማዶች ሳይበከሉ ሀገራዊ ሕሊና እና ጨዋነት ያለው አዲስ ትውልድ ለማፍራት በትጋት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሃይማኖት ሰንደቅ ጥላ ሥር መከፋፈልን እንደ ስኬት የሚቆጥሩ ድምፆች መበራከታቸውን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ ተቋማቱ በተስፋ መቁረጥ ማዕበል ውስጥ እንደ ጽኑ አለት በመቆም፣ በተከፋፈሉ ልቦች መካከል የመመካከር፣ የይቅርታ እና የእርቅ ሰባኪዎች በመሆን በጽናት እንዲቆሙ አስገንዝበዋል።
በቅርቡ በተካሄደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የእምነት ተወካዮች ሀገራዊ ስክነት እንዲመጣ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የተወጡት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ መስክረዋል።
መንግሥት ለእምነት ተቋማት ያለው ከበሬታ ከፍተኛ መሆኑን እና ነፃነታቸውን የማከበር እና የመጠበቅ ጽኑ አቋም እንዳለውም አረጋግጠዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: