Search

"ትልቁን በጀት ለትምህርት ዘርፍ በመመደብ ችግር ፈቺ እና በሥነምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት እየሠራን ነው" - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ማክሰኞ ነሐሴ 26, 2018 282

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለትምህርት ዘርፍ ትልቁን በጀት በመመደብ በዕውቀት የበለፀጉ እና በስነምግባር የታነፁ ተማሪዎችን ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት “ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮዎች” በሚል መሪ ቃል 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ዛሬ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት እና የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች የሚገመገሙበት እና የቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ጥራት ላይ በተሠራው ጠንካራ ሥራ የተማሪዎች ውጤት እያደገ መምጣቱን እና አሁን ላይ በከተማዋ የትምህርት ውጤት 33 በመቶ መሻሻል ማሳየቱን አብራርተዋል፡፡

ዋናው ኢንቨስትመንት ትምህርት ላይ መዋል አለበት በሚል እሳቤ አስተዳደሩ ከፍተኛውን በጀት ለዚሁ ዘርፍ ማዋሉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ ትውልድን ከመሰረቱ መገንባት ወሳኝ በመሆኑ ከቀዳማይ ልጅነት ጀምሮ በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን የተገኘው መሻሻል ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በቀጣይም ከዚህ የላቀ ውጤት ለማምጣት መምህራን እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግር ፈቺ የሆነ፣ በዕውቀት እና በዲሲፕሊን የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር በጋራ እና በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: