ከተጠናቀቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፊት ለፊት፣ ግርማ ሞገስ በተላበሰው የጉባ ተራሮች ሥር፣ ከተንጣለለው የንጋት ሐይቅ ባሻገር፣ በሚገማሸረው የግድቡ ፏፏቴ ሥር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በልበ ሙሉነት እና በተረጋጋ መንፈስ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያበስረውን ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ የሚያሳየው ይህ ምሥል፣ እጅግ ብዙ ምሥጢሮችን የያዘ ወደ ኋላ ብዙ ዓመታትን የሚወስድ እና የሚመልስ ከፎቶግራፍነት የዘለለ ጥልቅ የታሪክ ማኅደር ነው።
የዘመናት የጂኦ-ፖለቲካዊ ማዕበል ተንጦ፤ ተንጦ በስተመጨረሻም ጸጥ ማለቱን የሚያበስር ዝምተኛ አዋጅ ነው። ይህ ምሥል ታሪክ ነው፤ ይህ ምሥል ዘመን ነው፤ ይህ ምሥል የዘመናት ቁጭት፣ ብሶት እና የድል አክሊል በአንድነት የተሰባጠረበት ሕያው ሐውልት ነው።
በኩራት በተዘረጋው እጃቸው የሚያመላክቱት ያ ግዙፍ የኮንክሪት ግንብ፣ የድንጋይ እና የብረት ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን የዘመናት የዕንባ ዘለላ፣ የላብ ጠብታ እና የደም ዋጋ የተከፈለበት የነፃነት ዐውድማ ነው።
ዓባይን የማልማት ሕልም ከጽንሰ ሐሳብነት አልፎ በተግባር መሬት መሳሙን፣ የትውልድ የብሩህ ተስፋ ፀዳል ፍንትው ብሎ መፈንጠቁን ከዚህ የተሻለ የሚገልጽ ጣፋጭ ቋንቋ የለም።
ከዚህ ግርማ ሞገስ ያለው ምሥል ጀርባ፣ ዐይን በማያየው የታሪክ ማዕበል ውስጥ የዘመናት ሴራዎች ኩልል ብለው ይፈሳሉ። የሄንሪ ሙንዚንገር አሳሽ ቡድን የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ያደረገው የከንቱነት ጉዞ፣ የቱርኮች የስስት ምኞት፣ እና የግብጽ የዘመናት ማባሪያ የሌለው ጥንሰስ በዚህ የጉባ ተራራ ጀርባ ሲሰባሰቡ ይታያሉ።
ኢትዮጵያን ከውኃዋ ለማራቅ የተሸረበው ሴራ ትናንት የጀመረ አይደለም። የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለዚህ ፈሳሽ ወርቅ ያደረጉት መራር ተጋድሎ፣ በዲፕሎማሲው መድረክ ያፈሰሱት ዕንባ እና የዋጡት ቁጭት በምሥሉ ላይ እንደ ጥላ ያንዣብባሉ።
የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በግብጽ አቀናባሪነት ሲሰባሰቡ፣ ሲገናኙ፣ ሲፈርሱ፣ ሲዶልቱ፣ ሲያሴሩ፣ እና እንደ 1929 እና 1959 ያሉትን አግላይ የቅኝ ግዛት ውሎች በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም።
ኢትዮጵያ የገዛ ሀብቷን አልምታ ከድህነት አዘቅት እንዳትወጣ፣ ብድር እንዳታገኝ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሮቻቸውን ሲዘጉባት፣ የውጭ አጋሮቻቸውን አሰልፈው ፕሮጀክቶቿን ለማክሸፍ የሠሩት ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች ሁሉ፣ በዚህ ፎቶ ጀርባ እንደ ትዝታ ደመና ተበትኖ ይታያል።
ይህ ምሥል የደም እና የሥነ-ልቦና ጦርነት ማብቂያ ምዕራፍ ነው። በጉራ እና በጉንደት፣ እንዲሁም በሌሎችም ታሪካዊ የጦር አውድማዎች ላይ ኢትዮጵያውያን ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ደማቸውን ያፈሰሱት "ውኃችሁን አትነኩም" ለሚለው የትዕቢት ፖለቲካ ማስተባበያ ለመስጠት ነበር።
ግብጽ እና አጋሮቿ የጦር መሣሪያ ከማዝመት አልፈው፣ መንፈሳዊ አባቶችን በመላክ ውኃው እርኩስ እንደሆነ እና ኢትዮጵያውያን ከገዛ ሀብታቸው እንዲርቁ ያደረጉት ሥርዓታዊ የሥነ-ልቦ እና ጦርነት የዚህ ሴራ እጅግ አሳዛኝ አካል ነበር።
የተረገመ ውኃ እየተባለ ትውልድ በገዛ ወንዙ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ እርስ በእርሱ እንዲባላ፣ የውስጥ ባንዳዎችን እና ቅጥረኞችን በየአካባቢው በማስታጠቅ የተተገበረው የፋሾዳው የረቀቀ ሴራ ሁሉ፣ ዛሬ በዚህ ምሥል ፊት አፈር ድሜ በልቷል።
የውክልና ጦርነት በማስነሣት ሀገርን ከውስጥ ለማፍረስ የተደረገው ርብርብ፣ ኢትዮጵያ የሰላም አየር እንዳትተነፍስ የተዶለተው ሸፍጥ በሙሉ፣ በዚህ ጽኑ መሪ እና አይበገሬ ትውልድ ትከሻ ላይ ተሰብሮ ወድቋል።
ይህ ፎቶ እውነት ለሚያማቸው፣ ከሐቅ ለሚሸሹ እና ኢትዮጵያን ለዘላለም በድህነት ለማየት ለሚመኙ ታሪካዊ ጠላቶች እጅግ የበረታ የራስ ምታት እና ጥልቅ ሕመም ነው።
የዘመናትን የውክልና ጦርነት፣ የባንዳዎችን ክህደት፣ የውጭ ኃይሎችን ጫና እና የተወሳሰበውን የጠላት ሴራ ሁሉ በጀግንነት ተጋፍጦ፣ ትውልድን አሰባስቦ ግድቡን ከዳር ያደረሰው መሪ፣ ያንን ሁሉ የታሪክ ሸክም አራግፎ በኩራት ሲቀመጥ ማየት፣ የድል አድራጊነት የመጨረሻው ጫፍ ነው። ይህ ምሥል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በምንም ዓይነት የውጭ ጫና እንደማይደፈርስ የሚያረጋግጥ የተግባር ማኅተም ነው።
በፎቶው ላይ የሚታየው እርጋታ፣ ማዕበሉን አልፎ ወደብ የደረሰች መርከብን ዝምታ ያንጸባርቃል። ጠላቶቻችን ኢትዮጵያውያን ተረባርበው ሀገራቸውን እንዳይገነቡ በፈጠሩት የሥነ-ልቦና ውድቀት ውስጥ ሆነን እርስ በርስ ስንባላ የነበርንበት ያ የጨለማ ዘመን ማብቃቱን፣ የብርሃን ዘመን መባቱን ይህ ምሥል በጉልህ ይናገራል።
የዚህ ታላቅ ትውልድ ንቅናቄ እና የተጋድሎ መንፈስ በሕዳሴው ግድብ የድል ምዕራፍ ብቻ የሚገታ አይደለም። የዓባይን የዘመናት ቋጠሮ የበጠሰው፣ የተወሳሰበውን ሴራ ያመከነው እና የተስፋ መቁረጥን ትርክት የቀለበሰው ይኸው የትውልድ ኃይል፣ የተፈጥሮ እና የታሪክ መብቱ የሆነውን የቀይ ባሕርን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በተመሳሳይ የድል መንፈስ እውን ማድረጉ አይቀሬ ነው።
ልክ በጉባ ተራሮች ላይ የማይቻለውን አስችሎ፣ የብድር በሮች ሲዘጉ በገዛ ኪሱ የብርሃን ሐውልት እንዳቆመ ሁሉ፣ የባሕር በር ጥያቄውም በማንም ኃይል ሊቆም የማይችል ርትዓዊ እና ትክክለኛ ጉዞ በመሆኑ፣ በዚሁ የትውልድ ቁርጠኝነት፣ አንድነት እና የነቃ አመራር ግቡን ይመታል።
ታሪክ ራሱን ይደግማል፤ እውነት ሁልጊዜም አሸናፊ ነው፤ ይህ የፎቶ ሐውልትም የትናንቱ የውኃ ሉዓላዊነት ድላችን ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ የነገው የባሕር በር ስኬታችን ብሩህ ተስፋ ሆኖ ለዘላለም የሚኖር ሕያው ምስክር ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: