Search

የትውልድ ግንባታ መሠረት የሆነው የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ የሪፎርም ጉዞ

ረቡዕ ነሐሴ 27, 2018 189
ትምህርት የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ምሰሶ እና የነገዋን ሀገር የሚቀርጹ የሰው ሀብቶች ማፍሪያ ዋና ግንባር ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመደመር እይታ ላይ የተመሠረተው የመንግሥት የትምህርት ዘርፍ ፖሊሲ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ መሠረታዊ እና መዋቅራዊ የፖሊሲ፣ የነባር አሠራሮች እንዲሁም የእውቀት ሽግግር ማሻሻያዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
እነዚህ ሰፋፊ ተግባራት የትምህርት ተዳራሽነትን ከማስፋት ባለፈ፣ ትኩረታቸውን የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ የሥርዓተ-ትምህርት ማሻሻያ ማድረግ እና የተማሪዎችን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ማደራጀት ላይ አድርገዋል።
በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትና ያመጧቸውን አዎንታዊ ለውጦች ስንመለከት፣ የሀገራችንን ታሪክ፣ ባህላዊ እሴቶች እና ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ እድገትን ያገናዘበ አዲስ የትምህርት ማዕቀፍ ተቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል።
በዘርፉ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማካተት የሚሰጡ ትምህርቶች ከሀገራዊ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣሙ በመደረጉ፣ የተማሪዎችን ሀገራዊ ፍቅር እና ሥነ-ምግባር የመገንባት ሥራ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል።
 
ከዚህ ጎን ለጎን የቋንቋ እና የፈጠራ ክህሎትን ለማሳደግ በተሠራው ጥረት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች በሰፊው እንዲስፋፉ ተደርጓል።
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የነበረውን የማጭበርበር እና የስርቆት ባህል በመስበር እውነተኛ የተማሪዎችን እውቀት የመመዘን አሠራር መዘርጋቱ የዚሁ ሪፎርም ዋና አካል ነው።
በተለይም በ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ፈተናዎች በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጡ በማስቻል፣ ትምህርት በራሱ ጥረትና እውቀት ብቻ የሚገኝበት ፍጹም ፍትሐዊ አሠራር እንዲሰፍን ተደርጓል።
ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉና በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይስተጓጎሉ ሰፊ የሥርዓተ-ምግብ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም የትምህርት ቤት ምግባ ፕሮግራም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች በሰፊው በመተግበሩ የተማሪዎች የመማር ፍላጎትና ውጤታማነት ያደገ ሲሆን፣ ህጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው ለመደበኛ ትምህርት ዝግጁ የሚያደርጓቸው መሰረተ-ልማቶችም ተዘርግተዋል።
ሀገራችን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን በትምህርት ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲስፋፋ ተደርጓል።
የኮዲንግ እና የዲጂታል ክህሎት ሥልጠናዎችን በመዘርጋት ወጣቶች በዓለም አቀፍ የዲጂታል ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፣ የኦንላይን መማሪያዎች እና የላቦራቶሪ ቁሳቁስ አቅርቦትን የማሻሻል ሥራዎች ተከናውነዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ምርምር ተኮር እንዲሆኑ መዋቅራዊ ለውጦች ተደርገዋል።
የራስ-ገዝነት ሥርዓት በመዘርጋት ዩኒቨርሲቲዎች በበጀት፣ በአካዳሚክ እና በምርምር ነፃነታቸውን አግኝተው በገበያ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ የትምህርት ዓይነቶችን እንዲቀርጹ አቅጣጫ ተቀምጧል፤ ለአብነትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ-ገዝነት ተሸጋግሯል።
ምንም እንኳ አሁንም የትምህርት መሰረተ-ልማት ልዩነቶችን ማጥበብ እና የመምህራንን ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የተጀመሩት መዋቅራዊ ሪፎርሞች ኢትዮጵያን ወደተሻለ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።
በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: