Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ስምምነት መፈረሙን ገለጹ

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 219

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል ዛሬ መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ይህ አዲስ የሚቋቋመው ኩባንያ በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ደግሞ ለተቋሙ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ አስተዋፅኦ ያደርግበታል።

ይህ ተቋም ወደ ሥራ ሲገባ በባንክ ዘርፉ ውስጥ የሚታየውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን ችግር የሚቀርፍ ከመሆኑም በላይ፣ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ አቅርቦትን እንደሚያስገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ይህ አጋርነት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት፣ እንዲሁም በሀገራችን የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል። 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: