Search

የሃሳብ ልዩነትን ወደ ሀገር ግንባታ አቅም የመቀየር ጥበብ

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 142

ኢትዮጵያ የብዝኃ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ የዳበረ ባህል እና የረጅም ዘመን የጋራ ታሪክ ባለቤት ነች።

ይህ ውብ ብዝኃነት እና አብሮነት የጥንካሬያችን መሰረት ቢሆንም፤ በተለያዩ ዘመናት ምላሽ ያላገኙ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ እና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት እንዲሁም ለመተማመን መሸርሸር ምክንያት ሆነው ቆይተዋል።

አሁን ላይ ይህንን አዙሪት ሰብሮ በመውጣት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የህልውና ጉዳይ ሆኗል።

የሃሳብ ልዩነት መኖር በራሱ ችግር አይደለም። በዓለማችን ጠንካራ ዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ብልጽግና የገነቡ መንግሥታት ታሪክ እንደሚያሳየው፤ ዋነኛው የጥንካሬያቸው ሚስጥር ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ የውይይት የመፍታት ባህል ማዳበራቸው ነው።

ችግሩ የሚፈጠረው የራስን ሃሳብ ብቻ ፍጹም እውነት አድርጎ በመውሰድ የሌላውን ድምጽ ለማፈን ሲሞከር ነው።

"እኛ" እና "እነሱ" የሚለው ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ የጋራ ቤታችንን ከመጉዳት ባለፈ ያመጣው ትርፍ የለም።

ዴሞክራሲ የሃሳብ ተፎካካሪን እንደ ጠላት ሳይሆን፤ የተለየ አማራጭ ይዞ እንደቀረበ የአንድ ቤት ልጅ እንድንመለከት ያስተምረናል።

እውነተኛ ውይይት የራስን ሃሳብ ከመናገር ባለፈ የሌላውን የማዳመጥ ጥበብን በጥልቅ ይጠይቃል።

የተለየ አመለካከት መኖሩን መቀበል እና የሌሎችን ስጋት ለመረዳት ፈቃደኛ መሆን የራስን አቋም መተው ማለት አይደለም።

ይልቁንም ውይይት አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት የትግል ሜዳ ሳይሆን፤ ሁሉም ወገኖች የጋራ መፍትሔ የሚያፈልቁበት የድል አውድማ ነው።

ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚፈቱ ባለመሆናቸው የሁሉንም ወገን ንቁ ተሳትፎ ይሻሉ።

ሀገራችን ያካሄደችው ሀገራዊ ምክክርም የተለያዩ ድምጾች የተደመጡበት እና ለዘመናት ለተንከባለሉ ችግሮች የጋራ መፍትሔ የተጠቆመበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

መግባባት ማለት ሁሉም በአንድ ሃሳብ ላይ እንዲስማማ ማስገደድ ሳይሆን፤ ልዩነቶች እያሉም በጋራ እሴቶች ላይ ተመስርቶ አብሮ ለመኖር፣ ለመከባበር እና ችግሮችን ያለ ግጭት ለመፍታት የሚያስችል ጽኑ መሰረት መፍጠር ማለት ነው።

የሃሳብ ልዩነታችንን ወደ ጠላትነት ከመቀየር ይልቅ ለጋራ መማሪያነት ብንጠቀምበት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን።

የትናንትን ቁስል ወደ ነገ ተስፋ መቀየር የሚቻለው በመደማመጥ እና በጋራ መፍትሔ ፍለጋ ብቻ ነው።

ውይይት የድክመት ምልክት ሳይሆን፤ ልዩነቶቻችንን ወደ ጥንካሬ የምንቀይርበት የተሻለ የነገ መንገድ ነው።

ይህን ማድረግ ስንችል ማንም የማይገለልባት፣ ሁሉም በእኩል ክብር የሚኖርባት እና እውነተኛ ዴሞክራሲ የሰፈነባትን ጠንካራ ኢትዮጵያ ለትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: