Search

የዲፕሎማሲ እና የልማት ምዕራፍ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የኢትዮጵያ የቀጣናው መሪነት

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 168

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባቱ በአፍሪካ የሃይድሮ-ፖለቲካ፣ የኃይል ዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ትስስር ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነው።

ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የኅብረት እና የዕውቀት አስተዋጽኦ የተገነባው ይህ ታላቅ የዘመኑ ትውልድ ሀውልት ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ባለፈ የሀገራችን ትንሣኤ፣ የሉዓላዊነት መገለጫ እና የታሪካዊ ፍትሕ ማረጋገጫ ሆኖ ቆሟል።

በሳይንሳዊ አሰራር የሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሂደት የውኃ ፍጆታ የሌለው በመሆኑ ግድቡ የውኃ መጠንን ሳይቀንስ ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ወደ ታችኛው ተፋሰስ እንዲያልፍ ያደርጋል።

ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ከመልማት ውጭ የትኛውንም ወገን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት እና በፍትሐዊነት የመልማት ጽኑ መርህ እንዳላት በተግባር ያስመሰከረ ነው።

ለሱዳን እና ለግብፅ የጎርፍ አደጋን በመከላከል፣ የደለል መጠንን በመቀነስ እና የውኃ ትነትን በማስቀረት የዜሮ ድምር ጨዋታውን ወደ የጋራ ተጠቃሚነት ቀይሮታል።

ይህ አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት አካሄድ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት እና የቀጣናው መሪነት አቅም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ግድቡ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ኤሌክትሪክ ኤክስፖርት እስከ 51 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ በመሸፈን ሀገራችንን በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ገበያ ውስጥ ዋነኛ አቅራቢ አድርጓታል።

ንጹሕና ታዳሽ የአረንጓዴ ኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ መቻሉ የቀጣናውን የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከመደገፉም በላይ የኢኮኖሚ ትስስሩን በማይበጠስ ገመድ አስተሳስሮታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በዓለም አቀፍ ሕግ ደረጃ ጸድቆ በሥራ ላይ መዋሉ ለዘመናት የቆዩትን ፍትሐዊ ያልሆኑ የቅኝ ግዛት ውሎች በማክሰም፣ ቋሚው እና ሕጋዊው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን (NRBC) እንዲመሠረት አድርጓል።

ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም ሳትጎዳ አብሮ የመልማት መርሕን በመከተል የሰላም፣ የልማት እና የፍትሐዊነት ምሰሶ መሆኗን ለዓለም አስመስክራለች።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: