በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 28ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በአሶሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የክልሉ ዓመታዊ የትምህርት ጉባዔ እና ንቅናቄ “ጥራት እና ተደራሽነቱ የተረጋገጠ ትምህርት ለተሻለ የመማር ውጤት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው መደበኛ ትምህርትን ለሁሉም ከማዳረስ አንጻር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የመማሪያ መጻሕፍት አቅርቦት፣ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብርን ማጠናከር እንዲሁም የተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ማጠናከር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ያሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ውጤታማነትም እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ተማሪዎች መሠረታዊ ክህሎት እና ዕውቀት በመያዝ የፈጠራ ችሎታቸው ጭምር እንዲሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ሲሆን ይህም ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በተለይም የኦንላይን ፈተናዎችን በመተግበር ተማሪዎች ዲጂታል ክህሎታቸው እንዲሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲሱ ዓመትም የተማሪዎችን የፈተና ውጤት ለማሻሻል እና ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል የትምህርቱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ተግተው እንዲሠሩ አቶ አሻድሊ ሐሰን አሳስበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) ጉባዔው በ2018 የትምህርት ዓመት የተገኙ ስኬቶችን እና ችግሮችን ለይቶ በመምከር ቀጣዩን የ2019 የትምህርት ዘመን ውጤታማ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
በጀማል አሕመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: