Search

በ2018 የጀመረው የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አንደኛ ዓመት በስኬት ተጠናቅቋል - ኢትዮ ቴሌኮም

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 183

ኢትዮ ቴሌኮም የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ የአንድ ዓመት ጉዞ እና የሁለተኛ ዓመት ዕቅድን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ስትራቴጂው ለሦስት ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውሰው የመጀመሪያው ዓመት በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም 2018 እስከ 2020 . ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ የሦስት ዓመት አጠቃላይ የዲጂታል ልማት ዕቅድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ስትራቴጂው ከአንድ ተቋም ስኬት ባሻገር ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ግብን ያነገበ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መጫወት የሚያስችላት መሆኑን ተናግረዋል።

የዜጎችን ሁለንተናዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የሚሆነው ይህ ስትራቴጂ ዘርፈ ብዙ ተደራሽነትን በማረጋገጥ የቴሌኮም እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚያስችል መሆኑም ተነሥቷል።

የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ ትግበራ የመጀመሪያው ዓመት 215 ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘበት ነው። በስትራቴጂው ማጠናቀቂያ የደንበኞችን ቁጥር ወደ 90 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ ሲኖር፣ የቴሌብር ደንበኞችንም ቁጥር 60 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፣ የስትራቴጂው ግብ ኩባንያውን ከተለመደ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባንያ መቀየር ነው።

ደንበኛ ተኮር ዲጂታል አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተደገፈ የሥራ ቅልጥፍና፣ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የሰው ኃይል ማጠናከር እና ዘላቂነት እና አረንጓዴ ዕድገትን ማጠናከር የስትራቴጂው ዋና ዋና ግቦቹ ናቸው።

እስከ 2020 . ድረስ የቴሌኮም ተጠቃሚዎችን ቁጥር 100 ሚሊዮን ማድረስ፣ የቴሌብር ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 75 ሚሊዮን፣ 4G ሽፋንን ወደ 85% ማሳደግ እና 5G አገልግሎት ወደ ተጨማሪ ከተሞች ማስፋፋት እና የአሮጌ የኮፐር መስመሮችን በፋይበር መተካት ዋና ዋና ግቦች ናቸው።

ስትራቴጂው ከቁጥር ባሻገር ሰው ተኮር ልማት ነው ያሉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በመሆኑም ስትራቴጂው ሲጠናቀቅ 2.6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

በአብርሃም ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: