Search

የኢትዮጵያ ማንሰራራት በግብርናው ዘርፍ የታሪካዊ የምርታማነት ስኬት እና የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 145

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ታሪካዊ ስኬቶች የሀገራችንን ማንሰራራት በተግባር ያሳዩ ሆነዋል።

የዘንድሮው የጳጉሜ ቀናት መርሃ ግብር "የኢትዮጵያ ማንሰራራትበሚል መሪ ቃል የሚከበረው፣ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት የግብርና ውጤቶች ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ጠንካራ መሠረት መጣላቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን በማሰብ ነው።

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገው ሀገራዊ ጉዞ፣ ዛሬ በተግባር ፍሬ ማፈራት ጀምሯል።

ላለፉት አያሌ ዓመታት ሀገራችንን ሲፈታተን የነበረውን የምግብ ጥገኝነት በመስበር፣ በምግብ ራሷን የቻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕይ በተጨባጭ ውጤቶች እየተደገፈ ይገኛል።

በተለይም በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት፣ በክላስተር እርሻ አሠራር እና በአጠቃላይ የምርታማነት ማደግ በኩል የተመዘገቡት ውጤቶች ሀገራችን ወደ ተለየ ታሪካዊ የምርታማነት ምዕራፍ መሸጋገሯን ያመላክታሉ።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው የምርት መጠንም በኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚይዝ ነው።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (/) ይፋ እንዳደረጉት፣ በበጀት ዓመቱ 33.5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ማልማት መቻሉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ በመደረጉ፣ አርሶ አደሩ የመሬቱን ለምነት ለመጠበቅ እና ምርታማነቱን በእጥፍ ለማሳደግ አስችሎታል።

የሀገር ማንሰራራት የሚረጋገጠው በሰብል ምርት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ጤናማነት እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት በማረጋገጥ ጭምር በመሆኑ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍም የላቀ ውጤት ተመዝግቧል።

በዘርፉ በተለይም በወተት፣ በማር እንዲሁም በእንቁላል ምርት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

በሌላ በኩል የግብርናው ዘርፍ የሀገራችንን የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመደገፍ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ 4.55 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ለዚህ ስኬት ደግሞ የቡና ምርት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል።

ይህ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ሀገራችን ለልማት ሥራዎች የሚሆናትን ሀብት በገዛ ምርቷ እንድታፈራ ትልቅ አቅም ሆኗታል።

በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ይህ ታሪካዊ የምርታማነት እድገት፣ ሀገራችን ከጥገኝነት ወጥታ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን የኢኮኖሚ ነፃነት ጉዞ እውን የሚያደርግ ጠንካራ መሠረት ሲሆን፣ በዚህ የስኬት ጉዞ ውስጥም የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጎልቶ ይታያል።

በዓይናለም ሀድራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: