በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ታሪክ ውስጥ አዲስ ብሩህ ምዕራፍ ተከፍቷል! የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተመዝጋቢዎች ቁጥር 50 ሚሊዮን ማለፉ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ የምሥራች ነው።
ይህ ግዙፍ አኃዝ ኢትዮጵያ ዘመናዊ እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው ጉዞ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን የሚያሳይ ታሪካዊ ማረጋገጫ ነው።
ዓለም በዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሚመራ የቴክኖሎጂ ዘመን ውስጥ እጅግ ፈጣን ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ፉክክር ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ዲጂታል ቴክኖሎጂን እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመያዝ በትኩረት እየሠራች ነው።
ይህ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተቀባይነት ወደ አቅራቢነት በማሸጋገር የዲጂታል ዲፕሎማሲ እና የደቡብ-ደቡብ ትብብር መሪ እንድትሆን አስችሏታል።
የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ማለፉ የዚህን ትራንስፎርሜሽን መዋቅራዊ ለውጥ በግልጽ ያሳያል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የተበታተነ እና ወጥ ያልሆነ የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተገቢው መንገድ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ግን በቀን እስከ ሁለት ሚሊዮን ማረጋገጫዎችን የማስተናገድ አቅም የገነባው እና እስካሁን ከ190 ሚሊዮን በላይ ዲጂታል ጥሪዎችን ያስተናገደው የፋይዳ ሥርዓት፣ የተደረሰበትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ብስለት እና የሕዝብ አመኔታ በተጨባጭ ያረጋግጣል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፋይዳን ዋነኛ የደንበኞች ማንነት ማረጋገጫ (KYC) አድርጎ ማጽደቁ የፋይናንስ ተቋማትን አሠራር በእጅጉ አዘምኖታል።
ይህ ግዙፍ ስኬት ለ'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' ስትራቴጂ እውን መሆን መሠረታዊ የማፋጠኛ ሞተር ነው።
ፋይዳ እንደ ቀዳሚ የዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት በማገልገል፣ ማናቸውም የፋይናንስ እና የኤሌክትሮኒክስ ንግድ አገልግሎቶች በታማኝ የማንነት ማረጋገጫ ላይ እንዲገነቡ እያደረገ ነው።
በተለይም ከባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተፈጠረው ጠንካራ ትሥሥር የአገልግሎት ወጪን በ60 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፣ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት መስጫ መድረክ ከሆነው "መሶብ" ጋር በመቀናጀትም ከ185 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት በማቅረብ አስደናቂ የአሠራር ለውጥ አምጥቷል።
ይህ ሒደት መደበኛ የባንክ ሥርዓት ውስጥ ያልነበሩትን ዜጎች ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ በማካተት እና መደበኛ ያልሆነውን ጥላ-ኢኮኖሚ ወደ መስመር በማስገባት በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ይህንን ሀገር በቀል እና በክፍት ምንጭ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት "ፋይዳቨርስ" በተሰኘ ተቋማዊ ማዕቀፍ በኩል፣ ለሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት የተሞክሮ ማካፈል መጀመሯ ጥልቅ ስትራቴጂያዊ ትርጉም አለው።
በግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1321/2016 ሕጋዊ ዋስትና እና ከለላ ያገኘው ይህ መሠረተ ልማት፣ ወደፊት ለሚመጣው የ'ኤጀንቲክ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ' እና ለነጻ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ትሥሥር እጅግ አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
የዜጎችን ተጠቃሚነት እና መብት ያረጋገጠው ይህ የዲጂታል ሉዓላዊነት ጉዞ፣ ኢትዮጵያ የነገዋን አፍሪካ የቴክኖሎጂ ከፍታ በመቅረጽ በኩል የማይተካ ሚና እና የመሪነት ስፍራዋን በብቃት መያዟን በጉልህ ያሳያል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: