በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ምክትል ዋና ጸሐፊ ሙሐመድ አብዲ ዋሬ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመስክ ጉብኝት አድርጓል።
ምክትል ዋና ጸሐፊው በጉብኝታቸው ወቅት፣ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ የገነባችው አቅም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያደርጋት መሆኑን መስክረዋል።
ሁሉን አቀፍ ልማት እና ዕድገትን ለማስመዝገብ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ሙሐመድ አብዲ ዋሬ፣ ኢትዮጵያ ይህንን በመረዳት በሰው ኃይል ልማት እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሄደችበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ቴክኖሎጂውን በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና በፋይናንስ ዘርፎች በተግባር በመተርጎም ረገድ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ባለፈ ለአፍሪካ አህጉር ትልቅ አርአያ እና ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
የዚህ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጉብኝት ዋነኛ ዓላማም፣ የኢጋድ አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ ስኬታማ ተሞክሮ በመቅሰም፣ ቴክኖሎጂውን በየሀገራቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ውስጥ ማቀናጀት የሚያስችል ጠንካራ አህጉራዊ አጋርነት መፍጠር መሆኑ ተመላክቷል።
የልዑካን ቡድኑ አባላትም የኢትዮጵያን ልምድ በመውሰድ በዘርፉ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር)፣ ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ ዐበይት የምርምር እና የልማት ሥራዎችን አስመልክተው ለልዑካን ቡድኑ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያካበተችውን የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ተሞክሮ ለሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ለማካፈል እና በአጋርነት በጋራ ለመሥራት ሙሉ ዝግጁነት እንዳላት አረጋግጠውላቸዋል።
ይህ ስትራቴጂያዊ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት፤ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የዲጂታል ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር እና አባል ሀገራቱ የቴክኖሎጂ አቅምን በጋራ በመጠቀም ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑ ተገልጿል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: