ከታሪካችን ማኅደር ውስጥ አንዲት ገጽ እንግለጥ። ከዓመታት በፊት 'አንችልም'፣ 'አይሳካልንም' በሚል የሥነ-ልቦና እስር እና የውኃ ፖለቲካ ቁጭት ውስጥ የነበረች ሀገር፣ ዛሬ በገዛ አቅሟ ግዙፍ ግድብ ገንብታ ኃይል ማመንጨት መቻሏን ስናስብ፣ አንድ ትልቅ እውነት ቁልጭ ብሎ ይታየናል - ኢትዮጵያ ማንሠራራቷን መጀመሯ!
ዛሬ የማንሠራራት ቀን ብለን በሀገር አቀፍ ደረጃ ስናስብ፣ ዕለቱ የዘመን መለወጫ ዋዜማ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ሀገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት የጀመረችው እልህ አስጨራሽ የትንሣኤ ጉዞ ፍሬ ማፍራት የጀመረበትን ጽኑ ታሪካዊ እውነት የምንዘክርበት ዕለት ነው።
ይህ የኢትዮጵያ ማንሠራራት ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ በታላላቅ ፈተናዎች ማዕበል መሐል የተጠነሰሰ እና እያደገ የመጣ የለውጥ ጉዞ ነው። የዚህ የማንሠራራት ጉዞ ትልቁ ማሳረጊያ እና የነገው ብሩህ ተስፋ መነሻ የታየው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ የልማት የልብ ትርታ በሆነችው ታሪካዊቷ ስፍራ - ጉባ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት የዚህን ማንሠራራት ጥልቅ ትርጉም የሚያሳይ ነበር።
"የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የጉዟችን ማሳረጊያ ሳይሆን፣ የላቀ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መጀመሪያ ነው" በማለት፣ ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት አውጥተው ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ፣ በአጠቃላይ 30 ቢሊዮን ዶላር በጀት የሚጠይቁ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ይፋ አደረጉ። እነዚህም በታሪክ ማኅደር "7ቱ የጉባ ብስራቶች" በመባል ሰፍረዋል።
‘ብስራት’ የሚለው ቃል በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የረጅም ጊዜ ጥበቃን፣ ተስፋን እና አዲስ ብሩህ ዜናን የሚወክል ነው። የጉባ ብስራቶችም የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጡ የነገዋ ኢትዮጵያ ምሰሶዎች ናቸው።
አፍሪካን ከዓለም የሚያስተሳስረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦታ ጥበት የሚቀርፈው እና በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የቢሾፍቱ ሜጋ አውሮፕላን ማረፊያን ከመገንባት አንሥቶ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ኪሳራን የሚያስቀሩት የማዳበሪያ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች የዚህ ብስራት አካል ናቸው።
እንዲሁም የሀገራችንን ኃይል የሚያሟላው እና ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የተፈጥሮ ጋዝ ልማት፣ የዜጎችን ጥያቄ በመመለስ የከተሞችን ገጽታ የሚቀይረው የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ልማት፣ ለኢንዱስትሪ ሽግግር ወሳኝ የሆኑት ማዕድን ማውጣት እና ከሩሲያ ጋር በመተባበር የሚተገበረው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የዚህ ቃል ኪዳን አካላት ናቸው።
እነዚህ ብስራቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው።
ከሁሉም በላይ፣ የሕዳሴው ግድብ የሚያመነጨው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ለእነዚህ ግዙፍ የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ሞተር በመሆን፣ "የጉባ ብስራቶች" እና የሕዳሴው ግድብ እርስ በርስ የተመጋገበ ሚና እንዲኖራቸው ያደርጋል።
የማንሠራራቱ ራዕይ በወረቀት ላይ የቀረ ምኞት አይደለም። መንግሥት ፕሮጀክቶቹን ወደ መሬት ለማውረድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል።
ጳጉሜን 2ን በማንሠራራት መንፈስ ስናከብር፣ ዐይናችን ማረፍ ያለበት በቀጣዩ ወር፣ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ላይ በሚመሠረተው አዲሱ መንግሥት እና ከፊቱ በሚጠብቀው ታሪካዊ አደራ ላይ ነው።
የባለፉት 5 ዓመታት የማንሠራራት ጉዞ የነገውን ራዕይ በማውጣት፣ መሠረት በመጣል እና "አንችልም" የሚለውን ትርክት በመስበር ላይ ያተኮረ ከነበረ፤ ከመስከረም 30 በኋላ የሚመሠረተው አዲሱ መንግሥት ዋነኛ የቤት ሥራ፣ እነዚህን የ30 ቢሊዮን ዶላር "የጉባ ብስራቶች" ወደ መሬት ማውረድ እና የተደቀኑ ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር ነው።
ይህ ደግሞ አልጋ በአልጋ አይሆንም። የፋይናንስ አቅም ማነስ፣ የአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ውስንነቶች ከፊታችን ያሉ እውቅ ተግዳሮቶች ናቸው።
ስለዚህ አዲሱ መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) እና የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶች አጋርነት (የፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ) ስትራቴጂዎችን በስፋት መጠቀም እንዲሁም ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
የዛሬው የማንሠራራት ቀን፣ የባለፉት አምስት ዓመታት ትጋታችን ፍሬ ያፈራበትን የሕዳሴ ማማ የምናከብርበት ብቻ ሳይሆን፣ በጉባ የተበሰረውን አዲሱን የልማት ምዕራፍ አሻግረን የምናይበት የከፍታ ነጥብ ነው። ይህ የልማት አስተሳሰብ ለመላው ሀገራችን የዕድገት መንገድ፣ ለመላው አፍሪካ ደግሞ ተምሳሌት ነው።
የፖለቲካ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው፣ ድህነትን የጋራ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ፣ ሀገራዊ አቅምን በሙሉ ወደ ልማት ማዞር ከተቻለ፣ በጉባ የተበሰረው የብልጽግና ራዕይ በመስከረም 30ው አዲሱ መንግሥት አመራር ሰጭነት፣ ለትውልድ የሚሻገር የተግባር ሐውልት ሆኖ ይቆማል።
የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት፣ የልማት አጋሮች እና መላው ሕዝብ ይህን ታሪካዊ አደራ ከዳር ለማድረስ በጋራ የማንሠራራት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሠሩ ይገባል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: