የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለአዲሱ ዓመት ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት፣ ዜጎች ያለፈውን ዓመት በንጹህ ህሊና በጥልቀት በመገምገም ለተፈጸሙ ስህተቶች ይቅርታ በመጠየቅና ድጋሚ ላለመድገም በመወሰን አዲሱን ዘመን የመጽናናትና የመታደስ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው አዲሱ ዘመን የተሻለና ሰላማዊ እንዲሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ንቁ ተሳትፎና እውነተኛ መታደስ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በመካከላችን ትክክለኛ መግባባትና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ከስህተቶች ተምሮ በጽናት መቆም እንደሚገባም አብራርተዋል።
ልዩነቶችንና ችግሮችን ረጅም ጊዜ ሰጥቶ ቢሆን እንኳ በውይይትና በመግባባት መፍታት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀገራቸውን እንደ ጋራ ዕድልና ሀብት አድርገው በመቀበል በይቅርታ መንፈስ በአንድነት ተቃቅፎ ከመቀጠል ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።
ለችግሮች ሁሉ መድኃኒቱ ቅንና በጎ አሳቢ አእምሮ መያዝ መሆኑን የጠቆሙት ፓትርያርኩ፣ ሁላችንም ያሉብንን ጉድለቶች አርመንና አስተካክለን ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዘመን እንዲሆን የድርሻችንን እንድንወጣ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: