Search

የሺህ ዓመታት ሤራን በሕዳሴ የሰበረን ትውልድ ከቀይ ባሕር ማስቀረት አይቻልም

ማክሰኞ መስከረም 05, 2019 115

ኢትዮጵያ ከገዛ ምድሯ የሚመነጨውን የዓባይ ውኃ ለልማት እና ለብርሃን እንዳትጠቀምበት ለዘመናት ከተሸረቡ ውስብስብ ሴራዎች ጋር ስትታገል ኖራለች።

ለትውልዶች ሲሸጋገር የቆየው ይህ ጽናት እና ጥረት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት ተጠናቅቆ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ግዙፍ ታሪካዊ ክንውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያሳየው ትልቁ እውነት ቢኖር ኢትዮጵያውያን በጋራ ዓላማ ከተነሱ የማይበገር ኃይል እና የማይደፈር ሀገራዊ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት "ከሕዳሴ ግድብ በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ እና ከግድቡ በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ አንድ አይደሉም" በማለት የገለጹት እውነት፣ ይህንኑ የታደሰ ብሔራዊ ልዕልና የሚያረጋግጥ ነው።

ዘመናት የተሻገረውን ውስብስብ የዓባይ ፈተና በራሷ አቅም እና የገንዘብ ምንጭ መፍታት መቻሏ ለትልቅ አህጉራዊ ተጽዕኖ እና ለዲፕሎማሲያዊ የበላይነት መሠረት ጥሏል።

ይህንን ታሪካዊ ድል መሠረት በማድረግ፣ የቀይ ባሕር በር ጥያቄ ከፖለቲካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች አልፎ የኢኮኖሚ ሕልውና አጀንዳ ሆኖ ወጥቷል።

የዓባይን ዘመናት የተሻገረ ፍትሐዊ የመጠቀም ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ እና ቴክኒካዊ ብልሃት የፈታ ትውልድ፣ የባሕር በር እጦት የፈጠረውን ጫና ለመቅረፍ በጽናት ይሠራል።

ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ እና ታሪክ ከተቸራት ባሕር ውጭ እንድትቆይ የተደረገበትን ሁኔታ በሰላማዊ፣ በሕጋዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ማስተካከል የዚህ ትውልድ ቁልፍ ብሔራዊ ተልዕኮ ነው።

የባሕር በር ጥያቄው አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችለው ዋናው መሠረት ጥያቄው የተገነባበት ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ምሰሶ ነው።

ጥያቄው ታሪካዊ እና መልክዓ ምድራዊ መነሻ ያለው ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ሕግ እና ቀጣናዊ ስማምነቶች ድንጋጌዎች የተደገፈ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የቀረበው ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት እና ጥቅም በሚነካ አግላይ አካሄድ ሳይሆን ጎረቤቶችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ትስስር ስትራቴጂን የተከተለ ነው።

በስኬት ከተጠናቀቀው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚመነጨውን ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለቀጣናው ሀገራት ማቅረብ መቻሏ እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማትን የባለቤትነት ድርሻ ለመጋራት የተዘረጋው ማዕቀፍ በቀጣናው አዲስ የጋራ ዕድገት ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ፍትሐዊ እና አሸናፊ-አሸናፊ የመደራደሪያ አቅም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቷል።

በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕር፣ በባብ ኤል መንደብ እና በኤደን ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ የሚታዩት የደኅንነት እና የጂኦ-ፖለቲካ እውነታዎች የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ሚና ይበልጥ አስፈላጊ ያደርጉታል።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም የገነባችው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ በሕጋዊ መንገድ መገኘቷ፣ ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተገነዘበው ይገኛል።

ስለሆነም ከዓባይ ዳርቻ የተበሰረው የሕዳሴ ንጋት ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ መዘርጋቱ የታሪክ እና የተፈጥሮ እውነት ነው።

በሕግ፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ ተመሥርቶ የተጀመረው ይህ ጉዞ ኢትዮጵያን ቀጣናዊ የንግድ እና የኢኮኖሚ ማዕከል የሚያደርጋት ሲሆን፣ ለምሥራቅ አፍሪካም ዘላቂ ሰላም እና የጋራ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: