በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን የሚገኙ የጎፋ እና የኦይዳ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ የሆነው ‘ጋዜ ማስቃላ’ እና ‘ዮኦ ማስቃላ’ በዓል በመስከረም 13 እና 14 ቀን 2019 ዓ.ም በሳውላ ከተማ በልዩ ድምቀት ይከበራል።
በዓሉ የዘመን መለወጫ ከመሆኑ ባሻገር፣ የብሔረሰቦቹን ውብ ባህል፣ የኑሮ ዘይቤ እና ጥብቅ አንድነት ለዓለም የሚያስተዋውቅበት ታላቅ ሁነቶች አንዱ ነው።
ጋዜ ማስቃላ እና ዮኦ ማስቃላ በማኅበረሰቡ ዘንድ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የአብሮነት፣ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ እሴቶች በስፋት የሚንጸባረቁባቸው በዓላት ናቸው።
በተለይም በበዓሉ ወቅት የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት፣ ቂም እና በቀል በይቅርታ እና በመግባባት የሚተካበት እንዲሁም ለሕዝብ እና ለሀገር መልካም ምኞት የሚገለጽበት መድረክ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
የበዓሉ አከባበር የብሔረሰቦቹን የበለጸገ ባህላዊ ውርስ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሂደትን የሚያካትት ነው። በዝግጅቱም ላይ፦ የአባቶች ምርቃት እና የሕይወት ምክር፣ የደመራ ሥነ-ሥርዓት ማከናወን፣ የባህላዊ ዜማ እና ጭፈራ ትርዒቶች፣ የባህላዊ አልባሳት ውበት እና የምስጋና መግለጫዎች በዓሉን በላቀ ሁኔታ ያደምቁታል።
የመስከረም ወር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የዘመን መለወጫ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት ነው።
እንደ ወላይታ ጊፋታ፣ ጋሞ ዮ ማስቃላ፣ ጎፋ እና ኦይዳ ጋዜ ማስቃላ እና ዮኦ ማስቃላ እንዲሁም የጌዴኦ ዳራሮ ያሉ በዓላት ይዘዋቸው የሚመጡት መልካም እሴቶች በሕዝቦች ዘንድ ለጋራ መግባባት እና ለአብሮነት መጠናከር ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
በትዕግሥቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: