Search

የዋሽንግተንና ቴህራን ፍጥጫ በኒውዮርክ መድረክ ትራምፕ እና ፔዜሽኪያን በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ላይ ምን ይወስኑ ይሆን?

ሰኞ መስከረም 11, 2019 62

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሰባተኛ ወሩን በያዘበት በዚህ ወቅት፣ በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ያለው ውጥረት ከምንጊዜውም በላይ ተካርሮ ይገኛል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ጠባይዋን እንድታስተካክል ባስተላለፉት ጠንካራ ማስጠንቀቂያ "ኢራንን ማጥፋት፣ በኢኮኖሚ እንድትጎዳ ማድረግ ወይም ስምምነት ላይ መድረስ" የሚሉትን አማራጮች አስቀምጠዋል።

ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ጋር ለመገናኘት ፍላጎት ማሳየታቸው ለዲፕሎማሲያዊ ንግግር አዲስ በር ከፍቷል።

በሌላ በኩል ቴህራን ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የታገዱ ሀብቶቿ እንዲለቀቁና የተጣለባት የባህር እገዳ እንዲነሳ የሚያስገድዱ ሰባት ቅድመ-ሁኔታዎችን በካታር በኩል ልካለች።

የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤም አሜሪካ ግዴታዋን እስካልተወጣች ድረስ ስትራቴጂካዊው የሆርሙዝ ሰርጥ ተዘግቶ እንደሚቆይ አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁቲዎች ከአሜሪካ ጋር ላለመዋጋት መስማማታቸውን ቢገልጹም ኢራን ከሩሲያና ቻይና ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር ያለባትን ጫና ለመጋፈጥ እየሰራች ትገኛለች።

የዚህ ጦርነት መራዘም በአሜሪካ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ላይም ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል። የፎክስ ኒውስ አዲስ የህዝብ አስተያየት መስጫ ይፋ እንዳደረገው 71 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን አስተዳደሩ ግልጽ ስትራቴጂ የለውም ብለው እንደሚያምኑ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ጥናት ደግሞ 60 በመቶ የሚሆኑት የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ከመሰረቱ የተሳሳተ ውሳኔ እንደነበር መግለጻቸውን አስታውቋል።

አሁን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚያስተላልፉት መልእክት እና ለቴህራን ቅድመ-ሁኔታዎች የሚሰጡት ምላሽ የቀጣናውንና የዓለምን የወደፊት ሰላም ወይም የከፋ ውጥረት አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ የሚወሰን ይሆናል ተብል ይጠበቃል።

በሰለሞን ገዳ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: