ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘመናዊ፣ ብቁ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከያ ኃይል እየገነባች ከዘመኑ እኩል ፍጥነት እየተጓዘች ትገኛለች።
ታድያ ይህ ጉዞ የሚጀምረው ትጥቅን እና ሎጅስቲክስን በራስ አቅም ከማምረት እና ከማደስ ነው።
መዳረሻው ደግሞ ዘመናዊ መሣሪያዎች በአግባቡ ታጥቆ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጠብቅ ለጠላት የበጋ መብረቅ ለሕዝብ ደጀን የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው።
ይህ መከላከያውን ብሎም ሌሎች የጸጥታ ተቋማትን የመገንባት ሂደት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ተደማጭነት ያላት እና የሰላም ተምሳሌት የሚያደርጋት ነው።
የመከላከያ ኃይል ጥንካሬ የሚለካው በታጠቀው መሣሪያ ጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ያንን መሣሪያ በራሱ አቅም የማምረት እና የመጠገን አቅሙ ላይ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ኢንጂነሪንግ በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያሳየ ይገኛል።
ቀደም ሲል ለብዙ ዐሥርተ ዓመታት የቆዩ፣ የተበላሹ እና የወደቁ ታንኮች፣ ተሽከርካሪዎች፣ መድፎች እና ሮኬቶች አሁን በአዲስ መልክ እየታደሱ ነው።
ይህ ሂደት "ሪቨርስ ኢንጂነሪንግን (Reverse Engineering) በመጠቀም የተከናወነ ሲሆን፣ አሮጌ መሣሪያዎችን ወደ ዘመናዊነት ከመቀየር ባለፈ፣ የተኩስ አቅማቸውን እና ፍጥነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል። ይህም ኢትዮጵያ መሣሪያዎችን ከመግዛት ወጥታ ወደ ማሻሻል እና ወደ ማምረት መሸጋገሯን ያሳያል።
በተለይም በሰማይ ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ "ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ" መመሥረቱ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ተቋም የሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወይም ድሮኖችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ፈጥሯል። እነዚህ ድሮኖች ለስለላ፣ ለጥቃት እና ለደኅንነት ሥራዎች የሚውሉ ሲሆን፣ በከፍተኛ ከፍታ ላይ የመብረር ብቃት አላቸው።
እነዚህ ድሮኖች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዙ እና በሳተላይት ኮሙዩኒኬሽን የሚመሩ በመሆናቸው፣ ጠላት ሊያደርስ የሚችለውን የኤሌክትሮኒክስ መስተጓጎል (Jamming) የመቋቋም አቅም አላቸው።
ኢትዮጵያ ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባቷ፣ በዘመናዊ ውጊያ ውስጥ ያላትን የበላይነት የሚያረጋግጥ ነው።
ዘመናዊ መሣሪያ ብቻውን ሀገርን አይከላከልም፤ ያንን መሣሪያ በአግባቡ የሚጠቀም እና በዲሲፕሊን የታነፀ የሰው ኃይል የግድ ይላል። የመከላከያ ኃይሉ የግንባታ ስትራቴጂ ዋናው አካል ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባት ነው።
ፕሮፌሽናል ሠራዊት ማለት ከብሔር፣ ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት ወገንተኝነት የጸዳ፣ አጀንዳው ኢትዮጵያን መጠበቅ ብቻ የሆነ ኃይል ነው። ይህ ኃይል በከፍተኛ ወታደራዊ ሳይንስ እና ጥበብ የሠለጠነ፣ የቴክኖሎጂ እውቀት ያለውና በአካል ብቃት የበለፀገ ነው።
በተለይ የ"ኤሊት ፎርስ" (Elite Force) ወይም የኮማንዶና አየር ወለድ ሠራዊት ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። እነዚህ ሠራዊቶች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሰለጠኑ አሰልጣኞች አማካኝነት ጥብቅ ስልጠና ይወስዳሉ። የቀይ ቦኔት ባለቤት መሆን ከፍተኛ ክብርና ኃላፊነት ነው።
የኮማንዶ ሠራዊቱ በአየር፣ በባህርና በምድር በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተሰማርቶ ተልዕኮ የመፈጸም ብቃት አለው። ታድያ በልምምድ ወቅት የሚያሳዩት ብቃት የአካል ብሎም የአዕምሮ ጥንካሬያቸውን እና ብስለታቸውን የሚመሰክር ነው።
እነዚህ ወታደሮች የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን ድሮኖች እና ዘመናዊ መሣሪያዎች ተጠቅመው ውጊያን የሚያስቀሩ፣ ውጊያ ቢመጣ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድልን የሚያበስሩ ናቸው።
የመከላከያ ኃይሉ ጥንካሬ ዓላማው ውጊያ ሳይሆን ሰላም ነው። ጠንካራ መከላከያ መኖሩ ጠላት እንዳይደፍር ያደርጋል። ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ፣ ለቀጣናዊ ሰላም ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላም ምንጭ እንጂ የጦርነት ምንጭ ሆና አታውቅም በአንጻሩ ከጁባ እስከ ባይደዋ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም ዋጋ ከፍላለች። የሠራዊቱ መጠናከር ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ዋስትና ነው።
ሴት አየር ወለዶች፣ ኮማንዶዎች፣ የአየር ኃይል አብራሪዎች በብዛት መገኘታቸው ደግሞ የሠራዊቱን አካታችነትና ዘመናዊነት ያሳያል።
ሠራዊቱ ከቴክኖሎጂ ጋር ተስማምቶ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዘመናዊ ዶክትሪን ተመርቶ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል።
ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚሉት እንኳን ልትፈርስ ከፍ ትላለች የተባለውም በምክንያት ነው፤ ምክንያቶቹ ደግሞ እንደነዚህ ያሉ የሀገር ፍቅር በልባቸው የሚነድ እና የጀግኖች አርበኞች ልጆች በቴክኖሎጂ ተክነው በአቅም ላይ ብቃት ደርበው ድንበር እንዳይደፈር ጥቅም እንዳይነካ ሰንደቋን ይዘው ስለተሰለፉ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ግንባታ በስኬት እየተከናወነ ቀጥሏል፣ ፈተና አልበገረውም እንቅፋት አልስቆመውም። ሎጅስቲክስን እና ትጥቅን በሀገር ውስጥ የማምረት እና የማሻሻል አቅም ተገንብቷል። እየተገነባም ይቀጥላል።
ለዚህ ደግሞ ምስክሮቹ ሆሚቾ ተተኳሽ ማምረቻ "ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ" ናቸው። ይህንን ቴክኖሎጂ በአግባቡ የሚጠቀም፣ በዲሲፕሊን የታነፀና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስቀደመ ብቁ የሰው ኃይልም እየተገነባ ነው።
ዛሬ የምናየው መከላከያ የትላንቱን አሮጌ መሣሪያ አድሶ ለዛሬው ጦርነት ዝግጁ ያደረገ፣ የነገውን ቴክኖሎጂ ደግሞ ዛሬውኑ እያመረተ ያለ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ በፅናት ይጠብቃል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ እና ጥረት ብሎም በቴክኖሎጂ እና በእውቀት አስከብራ ታፍራ እና ተከብራ በነጻነት ታሪኳ አብባ ዛሬም ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች።
በሰለሞን ከበደ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: