Search

የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በቀይ ባህር ዙሪያ ተወያዩ

ሰኞ መስከረም 11, 2019 26

81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ (#UNGA81) ጎን ለጎን በኒውዮርክ የተካሄደው የሶስትዮሽ የምክክር መድረክ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየንን በአንድ መድረክ አገናኝቷል።

ይህ ከፍተኛ ስብሰባ እያደገ በመጣው የጂኦፖለቲካዊ ጫና እና ሁለንተናዊ ተፎካካሪነት ወቅት የብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር፣ የአፍሪካ እና የአውሮፓን ቁርኝት ማጎልበት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግጋትና የጋራ እርምጃዎች የበላይነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶበታል።

በስብሰባው ላይ በተለይም በቀይ ባህር፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በባህር ላይ ደህንነት ዙሪያ የተፈጠሩ ውጥረቶችና ስጋቶች የውይይቱ ዋና የትኩረት ማዕከል ሆነዋል።

መሪዎቹ በቀይ ባህር ቀጠና እና በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ ግጭቶች ይበልጥ እንዳይባባሱ ለመከላከል ቀጠናዊ ውይይቶችንና የሽምግልና ጥረቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማስከበር የጋራ አቋም ይዘዋል።

ይህም የቀይ ባህር ደህንነት ለቀጠናውና ለዓለም አቀፍ ንግድና ሰላም ያለውን ወሳኝ ሚና ያሳየ አበይት ውይይት ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ መድረኩ የአፍሪካን የልማት ፋይናንስ ፍላጎቶች ማሟላት እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅርን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን፣ ለልማት ባንኮች ተጨማሪ የገንዘብ አቅም መፍጠርና የአጀንዳ 2063 ስኬትን የሚደግፉ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማዘመን በሚቻልበት መልኩ በማዳበሪያ አቅርቦት እንዲሁም ሳተላይት ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ተደርሷል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: