Search

ከከፍታው ማማ እስከ ማይበገረው የጽናት መንፈስ በኢትዮጵያ የማድረግ አቅም እና ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት ውስጥ

ሰኞ መስከረም 11, 2019 119

በታሪክ አጋጣሚዎችና በዘመናት ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የዛሬዋን ጠንካራ ሀገር መገንባት ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለችግሮች ያለመንበርከክ፣ በፈተና ሳይበገሩ የማለፍ እና እንቅፋቶችን ተሻግሮ ድል የማድረግ የክብር መገለጫ ነው።

ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ፣ ከላሊበላ ድንቅ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ፣ ከሐረር የከተሜነት መነቃቃት፣ ከገዳ ሥርዓት የዲሞክራሲ እሴቶች እስከ ጎንደር እና የደቡብና ምዕራብ ክፍለ-ሀገራት ታሪካዊ የንግድና ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ድረስ ያለው ታሪካዊ መሰረት የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም በጥሩ ሁኔታ ያሳያሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የገጠሟታትን የውስጥና የውጭ ጫናዎች፣ ተፅዕኖና የዲፕሎማሲ ማነቆዎች ተቋቁማ የራሷን መንገድ መቅረፅ ችላለች።

የልማት ህልሟን ለማጨናገፍ የተሸረቡ ደባዎችንና ማዕቀቦችን በመሻገር፣ እራሷን በራሷ የማቀብ እና የማልማት እውነተኛ ጥራትን አሳይታለች።

ቀደም ሲል የህልውናዋ ዋስትና የምዕራባውያን እርዳታ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን እይታ በመቀየር በበጋ ስንዴ ልማት እና ሰፋፊ የእርሻ ስራዎች እራሷን ችላ ለሌሎችም የመትረፍ አቅም ላይ ደርሳለች።

በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም እና በልጆቿ ቁርጠኝነት ዳር ማድረስ እንደምትችል ማረጋገጫ ሆኗል።

በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር እና የከተሞች ኮሪደር ልማት ኢትዮጵያን የነገዋ አረንጓዴና ዘመናዊ አፍሪካ ተምሳሌት አድርጓታል።

ይህ የተገነባው የጽናትና የውጤታማነት ስነ-ልቦና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተፈላጊነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የጂኦፖለቲካዊ ጫናዎችን በአሸናፊነት የመወጣት ልምዷ በራሷ ሀብትና እውቀት የመልማት አቅሟ እንዲሁም ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በጽናት የመውጣት ታሪኳ ሀገራችንን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ ሊታለፍ የማይችል ዋና አጋር እና የወደፊት ተስፋ አድርጓታል።

የትናንት ፈተናዎች የዛሬ የከፍታ መሰላሎች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የማድረግ አቅሟን እያደሰች ወደታላቅ የብልፅግና ማማ ማምራቷን ቀጥላለች።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: