Search

"ማሽቃሮ"ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሰኞ መስከረም 11, 2019 42

የካፋ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነውን "ማሽቃሮ" በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የካፋ ብሔር ባሕል እና ቋንቋን የሚዳስስ ሲምፖዚየም እና የፓናል ውይይት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። በዓሉ በዞኑ እና ከዞኑ ውጪ በሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች እና እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በመድረኩ እንደገለጹት፣ ማሽቃሮ የካፊቾ ሕዝብ ከክረምት ዝናብ፣ ጨለማ እና ውጣ ውረድ አልፈው ወደ አዲሱ ዓመት ብርሃን መሸጋገራቸውን የሚያበስሩበት የምስጋና በዓል ነው።

ማሽቃሮ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የካፋ ነገሥታት መቀመጫ በነበረችው ቦንጋ (ቦንጊ ሸምበቶ) በፍቅር ሲከበር የኖረ፣ የካፋዎች ማንነት መገለጫ እና ታላቅ በዓል መሆኑን አመላክተዋል።

በዓሉ ማኅበረሰቡ ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም ከንጉሣቸው ጋር ሆነው የሚገመግሙበት፣ የተሻለ ሥራ የሠራ የሚሸለምበት እንዲሁም ደካማ ሥራ የሠራ የሚበረታታበት ባሕላዊ እና መንግሥታዊ ሥርዓት የተላበሰ ነው ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፣ ማሽቃሮ ከዞኑ አልፎ ለሀገር እና ለዓለም የሚተርፉ ዕሴቶችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል። የዞኑ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ለዘመናት እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድ የማሽቃሮ አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ 760 ሺህ ሄክታር በላይ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን መኖር ለዚህ አብነት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዞኑ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ / ታሪኳ ታከለ፣ የማሽቃሮን ዕሴቶች በመጠበቅ፣ በማልማት እና ለትውልድ በማሸጋገር በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እና የዘርፉን ሁለንተናዊ ፋይዳ ለማጎልበት እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሰለሞን ባረና

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: