በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀሰቀሱ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች መስተጓጎል እና የነዳጅ ዋጋ መናር በብዙ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ እቀባ እና ሳንካ በፈጠሩበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍ ባለ ጥንካሬ መቀጠሉ የሀገራችንን የማድረግ አቅም እና እያደገ የመጣውን አህጉራዊ ተፈላጊነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ኢኮኖሚው በበጀት ዓመቱ ከ10 ነጥብ 2 በመቶ በላይ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ መድረሱ ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ታላላቅ ሀገራዊ ራዕዮች እና ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በተግባር የመለወጥ ብቃቷን አረጋግጧል።
ለዘመናት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን የውጭ ንግድ ገቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጥ መቻሉ የዚሁ ተጨባጭ አቅም ዋና ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ከ1984 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት 17 ዓመታት ውስጥ ወደ ውጭ ልካ ያገኘችው አጠቃላይ የኤክስፖርት ድምር 11 ቢሊዮን ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ያንን የ17 ዓመታት አጠቃላይ ገቢ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ማሳካት የምትችልበት አቅም ላይ ደርሳለች።
ለአብነትም ከ1984 እስከ 2001 ባሉት 17 ዓመታት ከቡና ዘርፍ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 3.3 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ በተተገበሩት የአሠራር ማሻሻያዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘት ተችሏል።
በተመሳሳይ መልኩ ከ1984 እስከ 2011 ባሉት 27 ዓመታት ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 3.7 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እስከ 5.5 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ የ27 ዓመቱን ታሪክ በአንድ ዓመት አፈጻጸም በልጦ ማለፍ ተችሏል።
ይህ መዋቅራዊ ለውጥ ኢትዮጵያን ከዕዳ ጫና በማላቀቅ ለልማት የሚውል የውስጥ የፋይናንስ አቅምን እያሳደገ ይገኛል። የካፒታል ማርኬት እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ንግዱን በማፋጠን አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
የኢትዮጵያን የታሪክ ምዕራፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ የግብርናን እና የአገልግሎት ዘርፉን መቅደም የቻለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የማኑፋክቸሪንግ አቅም እያደገ ይገኛል።
በአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር በማስገባት አህጉራዊ ደረጃዋን ሁለተኛ ማድረግ የቻለች ሲሆን፣ በአንድ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ብቻ የ13 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈረሟ እና የ4 ቢሊዮን ዶላር የዳንጎቴ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት እያደገ የመጣውን ተፈላጊነት ያሳያሉ።
በግብርናው ዘርፍ በመስኖ ስንዴ ልማት እና በአግሮ-ፕሮሰሲንግ የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን ከስንዴ ዕርዳታ ፈላጊነት አላቆ ወደ ውጭ ላኪነት አሸጋግሯታል።
ይህ ስኬት ከውጭ ምርቶች ላይ የነበረውን ጥገኝነት ከመቀየሩም በላይ፣ ለውጭ እህል ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ሀገራዊ ጥንካሬን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ የማድረግ አቅም በታላላቅ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት ላይም በተግባር ተረጋግጧል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማረጋገጫ የሆነ ሲሆን፣ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋና የአቪዬሽን እና የሎጂስቲክስ ማዕከል ያደርጋታል።
ከዚህ ጎን ለጎን በሶማሊ ክልል የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ ፕሮጀክት፣ ፈጣን የመንገድ እና የኮሪደር ልማት፣ የከተሞች ውበት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች ኢትዮጵያን በፍጥነት እና በጥራት የመፈጸም አቅሟን ያረጋገጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ የማድረግ አቅም ከዕቅድ ባለፈ በተግባር የሚታዩ ስኬቶችን በመመዝገብ ከኢትዮጵያ ተሻግሮ ለሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማቀድ እና መፈጸም እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ እና አህጉራዊ አርአያ እየሆነ ይገኛል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: