የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥን (Tigray TV) መታገዱን ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በፕሬቶሪያ የተፈፀመውን የሰላም ስምምነት ተከተሎ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይትና በተደረሰበት ስምምነት መሠረት፣ ቀደም ሲል በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ወደ ሥራ መመለሱ ይታወቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች የሰላም ግንባታና የሙያ ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሚዲያው ወደ ሕገ-መንግሥታዊና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግራይ ቴሌቪዥን በተሰጠው ዕድል ተጠቅሞ እና የሙያ ሥነ-ምግባር አክብሮ አገልግሎት መስጠት ሲገባው፤ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ወደ ግጭት የሚገፋፉ እና ፅንፈኝነት የሚያበረታቱ መልእክቶች በተከታታይ እየተላለፉበት እንደሚገኝ የሚዲያ ይዘት ክትትል ግምገማችን ውጤት ያረጋግጣል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ፣ ከዛሬ ጀምሮ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን ይገልጻል።
ማሳሰቢያ፦
ማንኛውም ዲጂታል፣ የብሮድካስትም ሆነ የሕትመት ሚዲያ የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በህገወጥ መንገድ የሚያሰራጫቸውን ይዘቶች አሰራጭቶ ወይም አስተጋብቶ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ነው። ይህንን መመሪያ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሚዲያ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊና እርምጃዎች የሚወስድ መሆኑን አጥብቆ ያሳስባል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: