የከምባታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ 'መሳላ' በዓል አካል የሆነው 11ኛው የባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ እና የልማት ሲምፖዚየም 'መሳላ ለጋራ ዕድገታችን' በሚል መሪ ቃል በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፣ መሳላ የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ትስስር የሚታደስበት፣ ይቅር ተባብሎ አብሮነት የሚጎላበት ታላቅ የፍቅርና የሰላም መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው መሳላ የከምባታ ማንነት መገለጫ እና የሁሉም ነገር መነሻ መሆኑን አንስተው፤ ማኅበረሰቡ ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም ገምግሞ ለቀጣዩ ዓመት ዕቅድ የሚጋራበት የዕድገት ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በሲምፖዚየሙ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የብሔሩ ተወላጆች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
"የመሳላ እሴቶች ለከምባታ ማኅበራዊ ትስስር፣ ልማት እና ዘላቂ ሰላም" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ በምሁራን ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
የ2019 ዓ.ም የከምባታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ 'መሳላ' በዓል በነገው ዕለት በተለያዩ ደማቅ ሁነቶች በይፋ የሚከበር ይሆናል።
በአያንቱ እምሩ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: