የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በስፖርት ውርርድ እና ሎተሪ ዘርፍ ባካሄደው ምርመራ ፈቃድ ያላቸው ኦፕሬተሮች የፋይናንስ ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው መንግሥት ማግኘት የነበረበትን 27.5 ቢሊዮን ብር ገቢ እስካሁን እንዳላገኘ አስታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤዛ ግርማ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት ድርጅቶቹ ባንቀሳቀሱት 199 ቢሊዮን ብር ላይ 30 ቢሊዮን ብር የኮሚሽን ክፍያ ቢጠበቅባቸውም እስካሁን የከፈሉት 3.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው።
ሳይሰበሰብ ከቀረው ገቢ ውስጥ 8.64 ቢሊዮን ብሩ ዳሽ ቤት በተባለ የስፖርት ውርርድ ድርጅት ላይ የተከማቸ ዕዳ መሆኑን ረቂቅ የኦዲት ሪፖርቱ ያመለክታል።
መረጃው ረቂቅ የኦዲት ሪፖርት መሆኑን ያስገነዘቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የመጨረሻው የኦዲት ውጤት እንደተረጋገጠ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር ያልተከፈለውን ገቢ ለማስመለስ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዲጂታል ሎተሪን በሚመለከት ከግል አጋር ጋር የነበረው ስምምነት የሚጠበቁ የውል እና የቴክኖሎጂ ግዴታዎች ባለመሟላታቸው ምክንያት መቋረጡን አስረድተዋል።
የስፖርት ውርርድ እንቅስቃሴ መቆሙን በተመለከተ መንግሥት ዘርፉን በሕግ እና በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት የወሰደው የሪፎርም እርምጃ መሆኑን ወ/ሮ ቤዛ ጠቁመዋል።
አሠራሩ ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ መንግሥት በኦፕሬተሮች የፋይናንስ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ሙሉ እና ቀጥተኛ እይታ በሚኖረው አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ከተዋቀረ በኋላ የስፖርት ውርርድ በአዲስ መልክ እንደገና ይጀመራል ብለዋል።
የተቋሙን አቅም ለማሳደግም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሥራ ልምድ ያላቸው አዲስ የፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተመድበዋል።
በአሁኑ ወቅት የኦፕሬተሮች ፈቃድ ከተሰረዘ በኋላም የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ የውርርድ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ከፀጥታ፣ ከፋይናንስና ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሕጋዊ ፈቃድ በሌላቸው የስፖርት ውርርድ መድረኮች ላይ እንዳይሳተፍ እና ምንም ዓይነት የገንዘብ ግብይት እንዳይፈጽም አገልግሎቱ ጥብቅ ወ/ሮ ቤዛ አሳስበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: