Search

"ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያገኘችው ውጤት ለአፍሪካ ተምሳሌት ነው" - ICARDA

ሰኞ መስከረም 11, 2019 27

ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂንና ምርምርን መሠረት በማድረግ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካ አርአያ መሆኑን ዓለም አቀፉ የደረቃማ አካባቢዎች ግብርና ምርምር ማዕከል (ICARDA) ገለጸ።

ማዕከሉ ይህንን ያመለከተው የስንዴ ቴክኖሎጂዎችን ማሳደግ እና በአፍሪካ ዘላቂ የስንዴ ትራንስፎርሜሽን ለማስመዝገብ ብሔራዊ የዘር ሥርዓቶችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረው ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት ነው።

በአውደ ጥናቱ እንደተመላከተው፤ አፍሪካ ራሷን በምግብ ለመቻልና ሕዝቧን ለማበልጸግ እንደ ስንዴ፣ በቆሎ እና ካሳቫ ያሉ ቁልፍ ሰብሎችን ማምረት የሚያስችል ሰፊ የሚታረስ መሬት አላት። ሆኖም ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት ሁኔታ የግብርና ዘርፉን እየፈተነው ይገኛል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰብል ምርታማነት ላይ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም የሙቀት መጠን መጨመርን፣ ድርቅን እና በሽታዎችን የሚቋቋሙ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በስፋት በመጠቀም በኩል በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ያሳደገችበት ስልት ለአህጉሪቱ በምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ የሰብል ልማቱን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት፣ በበጋ የመስኖ ልማት በሚሊዮን የሚቆጠር ሄክታር መሬት በማልማት በስንዴ ምርት ራሷን ማበቃት ችላለች።

ይህ ስኬት የተገኘው በጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ፣ በሳይንሳዊ ምርምር እና በእርሻው ዘርፍ በተደረገ የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ድምር ውጤት መሆኑን ማዕከሉ አብራርቷል።

በባዬ ሙላት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: