Search

በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የተጻፈ ዲጂታል ሉዓላዊነት

ሰኞ መስከረም 11, 2019 32

የዘመናችን የቴክኖሎጂ አድማስ የሰው ልጅ አእምሮ ከፍታን ከሚለካባቸው ዋና መለኪያዎች አንዱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች የሚፈጥሩት ድንቅ አቅም ነው።

ዛሬ ሀገራት የፈጠራ አቅማቸውን የሚያሳዩበት እና የዲጂታል ሉዓላዊነታቸውን የሚያረጋግጡበት ዋነኛ መሣሪያ የድሮን ቴክኖሎጂ ሆኗል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በፕሮግራም ትዕዛዝ የሚመሩ የድሮን ስብስቦች በሰማይ ላይ በሚፈጥሩት ኅብረ ቀለም ታሪኮችን መንገር፣ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እና የዕድገት ደረጃን በግልጽ ማሳየት ችለዋል።

ቴክኖሎጂው የሳይንስ እና የሥነ ጥበብ ውህደት በመሆኑ የኢንጂነሪንግ አቅምን እና የፈጠራ ስኬትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ልዩ ጥበብ ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ከፍታ በቅርበት እና በተግባር እያሳየች የምትገኘው ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አስደናቂ የሰማይ ላይ የድሮን ትርኢቶችን እያቀረበች ነው።

በግንቦት ወር 2017 . በኢትዮ ቴክ 1 ሺህ 500 ድሮኖችን በመጠቀም በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ የታየው የመጀመሪያው ግዙፍ ትርኢት የዚህ ጉዞ ጠንካራ መሠረት ነበር።

ይህ ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ በጥር 2018 . የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90 ዓመት በዓል ሲከበር የቀረበው ማሳያ የተቋሙን የቴክኖሎጂ ሽግግር በግልጽ አሳይቷል።

በመስከረም 2019 . አዲስ ዓመት ዋዜማ ደግሞ 3 ሺህ በላይ ድሮኖችን በመጠቀም በሰማይ ላይ የተከናወነው አስደናቂ ትርኢት የዘርፉን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

የድሮን ትርኢቱ ከመዲናዋ አልፎ በወላይታ የጊፋታ በዓል ዋዜማም መታየቱ ቴክኖሎጂው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት በይፋ አስመስክሯል።

ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ያሳየቻቸው እነዚህ ትርኢቶች የስኬት ጉዞዎቿን የሚያንጸባርቁ ናቸው።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይ፣ የባሕር በር፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እና የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕይታዎች በሰማይ ላይ በደመቀ ሁኔታ ተስለዋል።

እንደ አዲስ ዓመት፣ የሕዳሴው ግድብ ምረቃ እና የተለያዩ በዓላት ላይ በድሮኖች አማካኝነት የተላለፉ መልዕክቶች የሕዝብን አንድነት፣ የልማት ስኬቶች እና የነገን ተስፋ የሚያደምቁ ናቸው።

በኢትዮጵያ በሰማይ ላይ በድምቀት የታዩት እነዚህ ድሮኖች በኢትዮጵያውያን ወጣት መሐንዲሶች እና ባለሙያዎች የበረራ አልጎሪዝም እና የቁጥጥር ሥርዓት የሚመሩ መሆናቸው ነው።

እንደ ኤሮ ዓባይ ባሉ ማዕከላት እየተመረቱ የሚገኙት ሀገር በቀል ድሮኖች ኢትዮጵያ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂው ዓለም ያስመዘገበችውን ግዙፍ መዋቅራዊ ለውጥ ያረጋግጣሉ።

ቴክኖሎጂን ከባህል እና ከሉዓላዊነት ጋር ማቀናጀት መቻሉ ኢትዮጵያ ከወረቀት ዕቅድ ወደ ተጨባጭ የኢንዱስትሪ እና የፈጠራ ከፍታ እየተሸጋገረች መሆኗን ያሳያል።

በሰማይ ላይ የሚስቡት እነዚህ ድንቅ ትርኢቶች የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን መሆን በግልጽ የሚያሳዩ፣ የትውልዱን የፈጠራ አቅም ያረጋገጡ እና የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት በላቀ ደረጃ ያስመሰከሩ ታሪካዊ ምዕራፎች ናቸው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: