በእስያ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ አህጉራት መካከል ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ የሆነው የቀይ ባሕር እና የባብ ኤል መንደብ መስመር በአሁኑ ወቅት የባሕር ላይ ውንብድና፣ የታጠቁ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ ማጠንጠኛ ሆኗል።
በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚያንቀሳቅሰው እና የዓለም አቀፍ ነዳጅ አቅርቦት ዋስትና የሆነው ይህ የውኃ መስመር በቀጣናው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ ለከፍተኛ ስጋት ተጋልጧል።
ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገቢ እና የወጪ ንግዷን የምታካሂደው በዚህ የቀይ ባሕር እና የኤደን ሰላጤ ኮሪደር በመሆኑ በባሕር መስመሩ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም የጸጥታ መደፍረስ በኢኮኖሚዋ እና በብሔራዊ ደኅንነቷ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ሀገራችን የባሕር ኃይሏን ማጠናከር "ምርጫ ሳይሆን የህልውና እና የግዴታ ጉዳይ" መሆኑን ይናገራሉ።
አዛዡ እንዳሉት በቀጣና የተፈጠረውን የጸጥታ ክፍተት ለመሙላት እና የንግድ መስመሩን ከወንበዴዎች እና ከግጭት ቀስቃሾች ለመታደግ ከኢትዮጵያ በበለጠ ይህንን አደጋ ተረድቶ የሚከላከል አቅም ያለው ኃይል የለም።
አካባቢው በአብዛኛው ደካማ የመንግሥት መዋቅር ባላቸው እና የጸጥታ ስጋት በሚታይባቸው ሀገራት የተከበበ በመሆኑ በባሕር መስመሩ ላይ አደጋ ሲያጋጥም የተቀናጀ የመከላከል አቅም ማነስ ይስተዋላል።
በተለይም የሁቲ ታጣቂዎችን እና የአል-ሸባብን መሰል ቡድኖች እንቅስቃሴ ለመግታት የየመን እና የሌሎች የባሕር ዳርቻ ሀገራት አቅም ማነስ፣ ለዓለም አቀፉ የንግድ መስመር ትልቅ ስጋት ደቅኗል።
የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር፣ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና በኢኮኖሚ አቅሟ በቀጣና ወሳኝ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኃይል ናት።
ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ከባሕር መዋቅር መራቋ በቀጣና የደኅንነት ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል።
ተንታኞቹ አክለውም፣ ጠንካራ የባሕር ኃይል የመገንባት አቅም ያለው አካል ከባሕር ደኅንነት ሥራ መገፋቱ ለቀጣናው ሰላም መደፍረስ ዋና ምክንያት መሆኑን ያመላክታሉ።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መጠናከር ለራሷ ብሔራዊ ደኅንነት ብቻ ሳይሆን፣ ለቀይ ባሕር እና ለባብ ኤል መንደብ የንግድ መተላለፊያ መስመር አስተማማኝ ዋስትና ይሆናል።
በባሕር ላይ የሚፈጸሙ የውንብድና ተግባራትን ለመከላከል እና ዓለም አቀፉን የንግድ ፍሰት ሰላማዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያላት ሚና ወደፊት ይበልጥ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አቅም መገንባት፣ በቀጣና ሰላምን ለማረጋገጥ እና ያልተረጋጉ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሚዛንን ለመጠበቅ እና የባሕር ንግድ መስመሩን ከማንኛውም ስጋት ለመከላከል ዝግጁ መሆኗን የባሕር ኃይል ግንባታው በተግባር እያሳየ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መጠናከር ለቀጣና ሀገራት "የጋራ መነቃቃትና የመተማመን" ምልክት በመሆኑ፣ የአካባቢው ሀገራትም ሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እርምጃ እንደ በጎ እና አስፈላጊ እርምጃ መደገፍ እንዳለባቸው ይገለጻል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: