የዛሬዋ ኢትዮጵያ በትናንት ትውልዶች ትጋት፣ መስዋዕትነትና የሀገር ፍቅር የተጠበቀች ናት።
የተረከባትን ሀገር እንዳለች ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን፣ ከተረከባት የተሻለች፣ የበለጸገችና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ዕድል የምትፈጥር ሀገር ማስረከብ የአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ትልቁ ኃላፊነት ነው።
ይህ ኃላፊነት በቃላትና በተስፋ ብቻ አይሟላም፤ የሚለካው በሥራ፣ በምርታማነት፣ በፈጠራና በውጤት ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ በሙያው ብቃት፣ በተጠያቂነትና በትጋት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ የሀገር ግንባታ አካል ነው።
በሥራ ቦታ የሚመረተው ምርት፣ በመስክ የሚገኘው ውጤት፣ ከፋብሪካ የሚወጣው ምርትና ለዜጎች የሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት በየዕለቱ የሚጻፍ የሀገር ግንባታ ታሪክ ነው።
የሀገር ልማት የሚፋጠነውም ያለንን ሀብትና አቅም በአግባቡ ወደ ጥቅም መቀየር ሲቻል ነው።
የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ መሬት፣ ውኃ እና ኃይል በተቀናጀ ዕቅድና በቴክኖሎጂ ሲደገፉ የኢኮኖሚ እሴት ይፈጥራሉ።
ሀብትን ወደ ጠቃሚ ምርት፣ ኢንዱስትሪን ወደ ሥራ ዕድል በመቀየር የሚገኘው ተጨባጭ የልማት ውጤት በዜጎች ኑሮ ይታያል።
በሀገራችን ያሉ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ማዕድን፣ ውኃና ሌሎችም ሀብቶች ከጥሬ ሀብትነት ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት መሸጋገር የሚችሉት በተገቢ ዕቅድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በካፒታልና በብቁ አፈጻጸም ሲደገፉ ነው።
የፕሮጀክት ውጤት የሚለካው በወሰደው ጊዜ ሳይሆን፣ ለሕዝብ በሚያመጣው ተጨባጭ ጥቅም ነው።
ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶቻችን የትውልድ ኃላፊነት በጋራ ጥረት እንዴት ወደ ተጨባጭ ውጤት ሊቀየር እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የረጅም ጊዜ ጥረትን፣ ሀገራዊ ተሳትፎንና የተቋማትን ጽናት የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።
ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በጥሩ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን፣ ዕቅዱን በተግባር በሚያውሉ ብቁ ተቋማት ነው።
ጊዜን፣ ጥራትንና ወጪን በአግባቡ መቆጣጠር፣ የሕዝብን ሀብት በኃላፊነት መጠቀምና የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት የትውልድ ኃላፊነትን ወደ ተቋማዊ ተግባር የሚቀይሩ መሠረቶች ሆነዋል።
የትናንት ትውልዶች ሀገርን በመስዋዕትነት እንደጠበቁ ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድ በሥራ የራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።
የተረከብናትን ሀገር የተሻለች ማድረግ ማለት ያለፈውን ታሪክ ማክበር ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ መነሻ መፍጠር ማለት ነው።
የዛሬ ትውልድ ታሪክ የሚጻፈው በሚዘክረው ታሪክ ብቻ ሳይሆን በሚገነባውና ለቀጣይ ትውልድ በሚያስረክበው ጠንካራ ሀገር ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: